በጅግጅጋ ከተማ የተገነቡ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ የተገነቡ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው
ጅግጅጋ፤ ሰኔ 14/2018(ኢዜአ)፦ በጅግጅጋ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ በመቀየር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ ።
የኮሪደር ልማት በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለኢንቨስትመንት ሳቢ እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ታቅዶ በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ትኩረት እየተተገበረ የሚገኝ ዘመናዊ የከተማ ልማት ስትራቴጂ ነው።
ይህ መርሃ ግብር የመንገዶችን ስፋትና ጥራት ማሻሻልን፣ የባቡርና የእግር ማቋረጫዎችን፣ የብስክሌት መንገዶችን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችንና የሌሊት መብራቶችን ማካተትን ታሳቢ ያደረገ ነው።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችው ጅግጅጋ፣ ከሀገር ውስጥ አልፎ ለቀጣናዊ የንግድና የኮሪደር ትስስር ያላት ስትራቴጂካዊ መገኛ እጅግ ከፍተኛ ነው።
በመሆኑም በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የጅግጅጋን መሠረተ ልማት በማዘመንና የንግድ እንቅስቃሴን በማቀላጠፍ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው።
ይህ የልማት እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ ደረጃ በደረጃ በመቀየር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከውበት ባለፈም ለከተማዋ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የንግድ አካባቢዎችን በማዘመን እና የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን በመጨመር የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑ ይገለጻል።
የጅግጅጋ ከተማን የኮሪደር ልማት በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የተከናወነው የልማት ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከመለወጡ ባለፈ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት አረጋግጧል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የፋፈን ዞን የሀገር ሽማግሌ ሱልጣን በደል አሌሊ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ በተከናወነባቸው መንገዶች ላይ ጤናማ የእግር ጉዞ ለማድረግና በቀላሉ ለመዝናናት ተችሏል።
በከተማዋ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት ፓርኮች ለጅግጅጋ ከተማ ተጨማሪ ውበትና ማራኪ ገጽታን የፈጠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የተገነቡት መሠረተ ልማቶች ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ ከአልባሌ ቦታዎች እንዲርቁና ለጤናቸው ተስማሚ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ በማገዝ ረገድም የጎላ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሱልጣን አላሌ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የተከናወኑት የኮሪደር ልማት ሥራዎች የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተገነቡት የመዝናኛ ሥፍራዎችም ነዋሪዎች በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱና እንዲዝናኑ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የጅግጅጋ ከተማ የኮሪደር ልማት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ባለፈ፣ የጎረቤት ሀገራት ነዋሪዎችንም የሚስብ ቀጣናዊ የመዳረሻ ማዕከል እያደረጋት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በጅግጅጋ ከተማ የተገነቡት የኮሪደር ልማት መሠረተ ልማቶች የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ የለወጡና ያሳመሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ መሐሙድ አሕመድ አብዲ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተገኘውን ሰላምና ልማት አጠናክሮ በመቀጠል፣ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ማስፋፋትና መደገፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሻፊ አሕመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ ከፍተኛ መነቃቃትን በመፍጠር፣ የከተማነት ደረጃዋን ከፍ ያደረገ፣ ገጽታዋን የለወጠ እንዲሁም ጽዱና ውብ እንድትሆን ያስቻለ ነው።
የኮሪደር ልማቱ በክልል ደረጃ በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሮ ወደ ሌሎችም ከተሞች እየሰፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ መርሃ ግብሩ የኅብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ ለከተማዋ ውበትና ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ታስቦ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።