በሸገር ከተማ በመኸር እርሻ እስካሁን ከ89 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ በመኸር እርሻ እስካሁን ከ89 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል
ሸገር ፤ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ በዘንድሮው የመኸር እርሻ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 89 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን የከተማ አስተዳደሩ የግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የሸገር ከተማ አስተዳደር በኢንዱስትሪና በከተማ ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በግብርናው ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
ከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወቅት አርሶ አደሩን በምርጥ ዘር፣ በማዳበሪያ እንዲሁም በትራክተር እገዛ በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
የከተማ አስተዳደሩ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአስተዳደሩ የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።
በከተማው በዘንድሮው የምርት ዘመን 95 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በማልማት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰበሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 89 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከታቀደው መሬትም 80 በመቶው በትራክተር የታረሰ እንደሆነም አክለዋል።
እስካሁንም ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ምርጥ ዘር መሸፈኑን ጠቁመው፣ አሁን ላይ ያለው ዝናብ ለእርሻው አመቺ በመሆኑ እንደ ገብስ፣ ስንዴና ማሽላ ያሉ የሰብል ዓይነቶች እየተዘሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብዓት አቅርቦትም ከታቀደው 162 ሺህ በላይ የአፈር ማዳበሪያ፣ 126 ሺህ መቅረቡንና ከዚህም ውስጥ እስካሁን 62 ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሮቹ መሰራጨቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል።
ዘርፉን በማጠናከር የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለመጠቀም በተሰጠው ትኩረት ቀደም ሲል በከተማዋ 7 ብቻ የነበሩትን የትራክተሮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 67 ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
እንዲሁም 80 ሺህ ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን አክለዋል።
በከተማው ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ አቅም እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።