ሁሉም ዜጋ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በላቀ ተነሳሽነት በመቀላቀል ለሀገር ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት -አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ዜጋ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በላቀ ተነሳሽነት በመቀላቀል ለሀገር ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት -አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ ፤ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ሁሉም ዜጋ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በላቀ ተነሳሽነት በመቀላቀል ለሀገር ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‘‘ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ቃል የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ምክትል ከንቲባና የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ሥራዎች ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለዘላቂ ልማት አይተኬ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የተሰራው ታላቅ ሥራ ዓለም አቀፍ እውቅናን ያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራው በተቋም ደረጃ ተደራጅቶ እየተሰራ መሆኑ ሥራውን ይበልጥ ስኬታማና ውጤታማ እንዳደረገው አብራርተዋል።
በዚሁ የአረንጓዴ ልማትና ውበት ሥራ አማካኝነት አዲስ አበባ በአፍሪካ ደረጃ በምሳሌነት የምትጠቀስ ከተማ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በላቀ ተነሳሽነት በመቀላቀል ለሀገር ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።