በአረንጓዴ አሻራ የተከናወኑ ተግባራት የአዲስ አበባን የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 24 በመቶ አድርሷል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ የተከናወኑ ተግባራት የአዲስ አበባን የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 24 በመቶ አድርሷል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ባለፋት አመታት በመዲናዋ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት የአዲስ አበባን የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 24 በመቶ ማድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‘‘ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ቃል የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ምክትል ከንቲባና የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ከተጀመረ ስምንት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በዚህም ሂደት ውስጥ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ባከናወናቸው ተከታታይ የልማት ሥራዎች የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋን 24 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
በቀጣይ ዓመታት የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ አመላክተዋል።
የምንተክለው ተስፋችንን፣ራዕያችንን እና ምግባችንን ነው ያሉት ከንቲባዋ ዛሬ ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ቃል ችግኞችን የምንተክለው ነገ የተሻለችና ብልጽግናዋ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመገንባት በመሆኑ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ፅዱ፣ውብና አረንጓዴ ከተማ ለመገንባት ከመትከል ባሻገር የተተከሉ ችግኞችን በየጊዜው መንከባከብና መጠበቅ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።