ግብጽ ከኒውዝላንድ ኬፕቨርዴ ከኡራጓይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ ከኒውዝላንድ ኬፕቨርዴ ከኡራጓይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ 12ኛ ቀኑን ይዟል።
በምድብ ሰባት ኒውዝላንድ ከግብጽ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ በቢሲ ፕሌስ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድቡ በተደረጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ኒውዝላንድ ከኢራን ሁለት አቻ ስትለያይ፣ ግብጽ ከቤልጂየም አንድ አቻ ወጥታለች።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
አፍሪካዊቷ ግብጽ ማሸነፍ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏን ያሰፋል።
በዚሁ ምድብ ቤልጂየም ከኢራን ምሽት አራት ሰዓት ላይ በሎስ አንጀለስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የመክፈቻ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች፣ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘም በምድብ ስምንት ኡራጓይ ከኬፕቨርዴ ነገ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት በሚያሚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አፍሪካዊቷ ሀገር ኬፕቨርዴ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ከስፔን ጋር ያለ ግብ አቻ በመለያየት የዓለም መነጋገሪያ ሆናለች።
በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ እየተሳተፈች የምትገኘው ኬፕቨርዴ በጥሩ ተነሳሽነት ላይ ትገኛለች።
ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ያላት ኬፕቨርዴ ማሸነፍ ከቻለች ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏ ሰፊ ይሆናል።
በመጀመሪያ ጨዋታዋ ሳዑዲ አረቢያ ጋር አንድ አቻ የተለያየችው ኡሯጓይ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ትጫወታለች።
በዚሁ ምድብ ስፔን ከሳዑዲ አረቢያ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በአትላንታ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሁለቱም ሀገራት በውድድሩ ላይ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።