በሊጉ የ36ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሊጉ የ36ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14/ 2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ መቻል ከኢትዮጵያ መድን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
መቻል በ53 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ መድን በ46 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው መቻል የአሸናፊነትን መንገድ ለማግኘት ይጫወታል።
በ35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 የረታው ኢትዮጵያ መድን ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
መድን የአምና የሊጉ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ምድረ ገነት ሽሬ በ37 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ49 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ምድረ ገነት ሽሬ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ጨዋታውን ማሸነፍ ይኖርበታል።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ሌላኛው የዕለቱ መርሐ ግብር ሃዋሳ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማን ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያገናኛል።
ሃዋሳ ከተማ በ48 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ46 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
በ35ኛ ሳምንት በነገሌ አርሲ 2 ለ 1 የተሸነፈው ሃዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ባህር ዳር ከተማ የድል መንገዱን ለማግኘት ይፋለማል።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች (19 ጊዜ) አቻ የወጣ ቡድን ነው።
ከቀኑ 10 ሰዓት መቀሌ 70 እንደርታ ከአዳማ ከተማ በአበባ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በ36 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አዳማ ከተማ በ42 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ የወጣው መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅበታል።
በ35ኛ ሳምንት ኢትዮዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 1 የረታው አዳማ ከተማ ዛሬ ካሸነፈ በሊጉ የመቆየት እድሉን ይበልጥ ያሰፋል።
ጨዋታው ላለመውረድ እየተደረገ ባለው ፉክክር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።