ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ስኬት ከመገናኛ ብዙኃን አመራር አባላትና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ስኬት ከመገናኛ ብዙኃን አመራር አባላትና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን ለማሳካት የሚያስችል ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር፣ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም እና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) መገናኛ ብዙኃን እስካሁን ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙኃን ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክሩን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም ማኅበረሰብ ለማንጸባረቅ መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ያለማንም ጣልቃ ገብነት አስፈላጊውን ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝና ምክክሩ አሁን ላይ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል።
ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም፤ ምክክሩ ሀገርን የምናሻግርበት፣ ለልጆቻችን ሰላም የሰፈነባትና የተረጋጋች ሀገር ለማስረከብ የምንሰራበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ይህ ምክክር የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው፤ የምክክሩ ስኬታማነት ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዮሐንስ ሽፈራው (ዶ/ር) በመድረኩ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን መገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በተከተለ መልኩ መዘገብ እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለዚህም መገናኛ ብዙኃን ሊከተሏቸው የሚገቡ ዓለም አቀፍ የአዘጋገብ ስልቶችና ሙያዊ ሥነ-ምግባሮችን ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ አመልክተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱን በሰፊው በማስተዋወቅና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በራሱ የውስጥ አቅም ያዘጋጃቸውን 15 የክልል የምክክር መድረክ ዘጋቢ ፊልሞች፣ 19 የቴሌቪዥንና የማህበራዊ ሚዲያ የቅስቀሳ መልዕክቶችን፣ 6 የሬዲዮ መልዕክቶችን እንዲሁም በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጫር መልዕክቶችን ለመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላት አስረክቧል።
ከሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መገናኛ ብዙሃን መልዕክቶቹን ወደ ሕዝብ እንደሚያደርሱ ተመልክቷል።