ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት በጦር ሜዳ ጠላትን ድል ከመንሳት ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ የሚወጣ የህዝባዊነትና የደግነት ምንጭ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦መከላከያ ሰራዊት በጦር ሜዳ ጠላትን ድል ከመንሳት ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ የሚወጣ የህዝባዊነትና የደግነት ምንጭ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር የተመሰረተበትን 4ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ታላላቅ መርሃ ግብሮች አክብሯል። 


 

በበዓሉ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የሰራዊቱ የጀግንነት ታሪክ እንደ ውቅያኖስ የማይነጥፍ ከመሆኑም በላይ፣ በጭና ግንባር የተቀዳጀው ድል የጠላትን ፖለቲካዊና ወታደራዊ አቅም ሙሉ በሙሉ የሰበረ የድል ማህተም ነው።

ሰራዊቱ በጦር ሜዳ ጠላትን ድል ከመንሳት ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ የሚወጣ የህዝባዊነትና የደግነት ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለዚህም ማረጋገጫው የሰራዊቱና የህዝቡን ጠንካራ አንድነት የሚያሳየው የ"ጭና ሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ" መገንባቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በጦር ግንባር የተሸነፈው የቀድሞው ሕወሓት እና ተላላኪዎቹ አሁንም የህዝቡን ሰላም ለማወክ በቅዥት እየተፈራገጡ መሆኑን ያነሱት አስተባባሪው፤ ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ታሪክ መስራትና ሀገር ማዳን ልማዱ በመሆኑ የአጥፊ ቡድኖች ህልም መቼም ቢሆን እንደማይሳካ አረጋግጠዋል።

የ403ኛ መከታ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል አዘዘው መኮንን በበኩላቸው፤ ኮሩ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተደቀኑ የጥፋት ፈንጂዎችን በተግባር በማምከን ከፍተኛ የሀገር ባለውለታነቱን እንዳስመሰከረ ገልጸዋል።


 

በሰሜኑ ህግ ማስከበር ወቅት የቀን ፀሀይ፣ የሌሊት ቁር፣ ጋራና ሸለቆ ሳይበግረው የጠላትን ሀገር የማፍረስ ህልም መና ማስቀረቱን፤ በሁሉም ግንባሮች በፈጸመው ተጋድሎ ኢትዮጵያን ከመፍረስ፣ ህዝቦቿን ደግሞ ከብተና መታደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 

በተጨማሪም መንግስትና ህዝብ የጣሉበትን አደራ በብቃት በመወጣት ጠላትን አሳፍሮ የመለሰ ታሪካዊ ኮር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዛሬም ቢሆን ጽንፈኛውንና ተላላኪዎቹን በማንኛውም ሁኔታ መመከት የሚችል ጽኑ ሰራዊት መገንባቱን ገልጸዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በበኩላቸው፤ የቀድሞው የህወሓት አንጃ በጭና ምድር ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው እኩይ ተግባርና የጭካኔ ድርጊት መፈጸሙን አስታውሰዋል።


 

ሆኖም የ403ኛ መከታ ኮር የምዕራብ ኮሪደርን በማስከፈት፣ የጥፋት ኃይሉ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ሲንቀሳቀስ በጭና ምድር ላይ ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ማድረጉን ገልጸዋል። 

ሰራዊቱ በልማት ስራዎችም በመሳተፍ እውነተኛ የህዝብ ልጅነቱን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም