ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ራሱን ዘመኑን በዋጀ ትጥቅና የሰው ሃይል እየገነባ ነው - ሌተናል ጀነራል መሰለ መሰረት 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦የሀገር መከላከያ ሰራዊት ራሱን ዘመኑን በዋጀ ትጥቅና የሰው ሃይል እየገነባ መሆኑን የመከላከያ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል መሰለ መሰረት ገለጹ።

የመከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር የተመሰረተበትን 4ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል።


 

የመከላከያ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል መሰለ መሰረት እንደገለጹት፤ ተቋም የሚገነባው በዱላ ቅብብል ነው።

የመከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር እንደ ስሙ የኢትዮጵያ መከታ መሆን የጀመረው ሰራዊት የተገነባበትን አካሄድ በመውረስ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርና ግዙፍ ሰራዊት ያላት መሆኗን በመጥቀስ፣ የተቋሙን የጀግንነት ስራዎች በተለያዩ መንገዶች መሰነድ እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዘመኑን በዋጀ ትጥቅና የሰው ሀይል እየተደራጀ መሆኑን ገልጸው፤ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ጥያቄና ፍላጎት አለው ያሉት ሌተናል ጀነራል መሰለ፤ ሰራዊቱ ብዙ ግዳጅ እንደሚጠብቀው በማሰብ መዘጋጀት እንዳለበት ገልጸዋል።

ሰራዊቱ የሀገር ውስጥ ባንዳና ተላላኪዎችን በፍጥነት መልክ በማስያዝ ለዋናው ተቋማዊ ግዳጅ መዘጋጀት አለበት ብለዋል።

ሰራዊቱ በየጊዜው በሚጎናጸፈው  ድል ሳይዘናጋ ለነገ የተሻል ስራ ራሱን ማጠናከር አለበት ብለዋል።


 

የዕዙ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል መሰለ በለጠ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሏል፣ ደም ፈሷል አጥንት ተከስክሷል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣትም ታሪኩን በአግባቡ መሰነድና ለትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

ሰራዊት በታሪክ ይገነባል፣ በዚህም ታሪኩን ሰንዶ ለትውልድ ያስተላልፋል ብለዋል።

ፈተናዎች ጀግኖችን ይወልዳሉ፣ ጀግኖችን ያፈራሉ ያሉት ሜጀር ጀነራል መሰለ በለጠ፣  የሰራዊቱ ክፍሎች የሰሩትን ታሪክ ለትውልድ በማስተላለፍ ታሪካቸውን ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም