ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ቀጥለዋል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የፀሐይ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሲዳማ ክልል ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ሆኮ ወረዳ የሆዲ ቦኩ ከተማ አነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በፕሮጀክቱ ምረቃ ወቅት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም የማህበረሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉት ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
የዚሁ አካል የሆነውና በ230 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሆዲ ቦኩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 525 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ከ2 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ከበደ ጋኖሌ በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቱ ወደ ሥራ መግባት የአካባቢውን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የኃይል አቅርቦቱም የሕብረተሰቡን የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ለማሻሻል ያስችላልም ብለዋል።
እንዲሁም ኢኮኖሚውን በማነቃቃት የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያሳድግና ለከተማዋ ዕድገት የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ክንፈ ነጋሽ በበኩላቸው፣ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ለታዳሽ ኃይል ልማት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተለይም ከመደበኛው የኤሌክትሪክ መስመር የራቁ አካባቢዎችን የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ በመገንባት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት በመላ አገሪቱ 43 የታዳሽ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በመገንባት ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
525 ኪሎ ዋት የሚያመነጨው የዛሬው የሆዲ ቦኩ ፕሮጀክት የውስጥ ለውስጥ መስመር ዝርጋታና ሦስት ትራንስፎርመሮች እንዳሉትም አስረድተዋል።
በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።