ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/ 2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ36ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ከነገሌ አርሲ ጋር አንድ አቻ በመለያየት የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል።

ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ብርሃኑ በቀለ በመጀመሪያ አጋማሽ ማብቂያ ላይ ያስቆጠረው ጎል ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል።

በረከት ወልዴ በ76ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ ላይ ባሳረፈው ጎል ነገሌ አርሲ አቻ ሆኗል።

የነገሌ አርሲው ቦና ቦካ በ16ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ65 ነጥብ ሁለት ጨዋታ እየቀረው ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል።

ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ በአንጻራዊነት ወጥነት ያለው አቋም ያሳየ ሲሆን ለበርካታ ሳምንታትም የሊጉ መሪ ሆኖ ቆይቷል።

ሲዳማ ቡና ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣይ ዓመት በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።

በሌላ በኩል ሲዳማ ቡና ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር የኢትዮጵያ ዋንጫን ለማንሳት ይፋልማል። ቡድኑ ዓመቱን በሁለት ዋንጫ የማጠናቀቅ እድል አለው።
ነገሌ አርሲ በ57 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ሸገር ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።

አብዲሳ ጀማል በ19ኛው እና አብዱልሰላም ዩሱፍ በ84ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ከዘጠኝ የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ በ38 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

በሊጉም ስምንተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሸገር ከተማ በ44 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።

ዛሬ በተደረገ የ36ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ ቡና ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የ36ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም