ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የፍትህ ዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዳማ፣ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ሕግ ምርምርና ፍትሕ ኢንስቲትዩት የፍትህ ዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ የፍትህ ሪፎርሙን ለማሳካት ያካሄዳቸውን የምርምር ውጤቶች በግብዓት ለማዳበር የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ገዛሊ አባ ሲመል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በጥናትና ምርምር የተደገፉ የመፍትሔ ሐሳቦችን እያቀረበ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ በቁልፍ የፍትህ ዘርፍ ጉዳዮች ዙሪያ የተከናወኑ አምስት የተለያዩ የምርምር ውጤቶች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

ምርምሮቹም የፍትህ አካላት ስነ-ምግባር፣ የፌዴራልና የክልል የህግ ተፈፃሚነት ወሰን ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች፣ በፍትህ ዘርፉ የዲጂታል አገልግሎት ዘመን የቋሚና ተዘዋዋሪ ችሎት አስፈላጊነት፣ እንዲሁም የህግ ትርጓሜና የተፈፃሚነት ወሰን የተመለከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ የምርምር ውጤቶች ጠንካራ የፍትህ ስርዓት በመገንባት በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የፍትህ ዘርፍ ሪፎርም ለማሳካት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም በህግና በአሰራር ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች ለመድፈን በእጅጉ ያግዛሉ ብለዋል።

የኦሮሚያ ህግ ምርምርና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አዱኛ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የፍትህ ስርዓትን ለማሻሻል እስካሁን ከ100 በላይ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ በግብዓትነት እንዲያገለግሉ ማድረጉን ጠቁመዋል።


 

በተለይም በዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርምና የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ስራዎችን ለማሳለጥ በጥናትና ምርምር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የፍትህ ስርዓቱን አሰራር ለማዘመንና በቴክኖሎጂ ለመምራት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች ለዛሬው መድረክ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከጥናትና ምርምር ስራዎች ጎን ለጎን፣ ብቁ የፍትህ አካላትን ለማፍራትና ጥራትን ለማረጋገጥ ለህግ ባለሙያዎች የስልጠናና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሯ አክለዋል።


 

በመድረኩ ላይ በፌዴራልና በክልል የሕግ ወሰን ተፈጻሚነት ዙሪያ የተካሄደውን ምርምር ያቀረቡት አብዲሳ ጉርሜ (ዶ/ር)፤ የጥናቱ ውጤት በፌዴራልና በክልል የሕግ ተፈጻሚነት ረገድ የሚታዩ ውስንነቶችን በግልጽ በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከቱን አስገንዝበዋል።

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ከፌዴራል ፍትህ ኢንስቲትዩት የተጋበዙ ተመራማሪዎችና የህግ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም