ቀጥታ፡

በስርዓት የተገነቡና ለህዝብ ቅርብ የሆኑ ተቋማትን የመፍጠር የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በስርዓት የተገነቡና ለህዝብ ቅርብ የሆኑ ተቋማትን የመፍጠር የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት ዛሬ በተቋማት ከሚሰሩ የሪፎርም ስራዎች መካከል በደንብ ማስከበር ባለስልጣን በተቋም ግንባታ እና የሰው ሃይል ልማት በ10 ዙር ሲሰለጥኑ የነበሩ ኦፊሰሮችን ባስመረቁበት ወቅት ነው።


 

ይህ የአቅም ግንባታ ስልጠና ኦፊሰሮቹ ከህዝብ ጋር አክብሮት የተሞላበት ተግባቦት እንዲኖራቸው፣ ህግና ስርዓትን ያለአንዳች አድልዎ እንዲያስከብሩ፣ ፍፁም አገልጋይነት እንዲላበሱ እና ስነምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

ከንቲባዋ ለደንብ ማስከበር ኦፊሰሮቹ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሲያገለግሉ ህዝባቸውን በፍቅር፣ በትህትና እንዲሁም በማክበርና ደንቦችን ያለ ምንም ርህራሄና ያለአድልዎ በማስከበር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

ተቋሞቻቸው በስርዓት የተገነቡ፣ ጠንካራ የአገልግሎት ስርዓት ያላቸው፣ ስነ ምግባር የተላበሱና አገልጋይ እንዲሁም ለህዝብ ቅርብ የሆኑ ባለሙያ እና አመራር የመፍጠር ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ከተማዋ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ፣ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ወታደራዊ አለባበስ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ እንዲሆን ሲጠቀሙበት ከነበረው የደንብ ልብስ ተጨማሪ ሆኖ የሚያገለግል አዲስ የደንብ ልብስ ይፋ መደረጉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም