ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የሲቪል ሰርቪስ ውጤታማ ሪፎርም የአገልግሎት ጥራት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦  የመደመር መንግሥት የሲቪል ሰርቪስ ውጤታማ ሪፎርም የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፋናን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ''ዲጂታል ለልህቀት'' በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ የሪፎርም ውጤቶችን የሚያሳየውን ኤግዚቢሽንና ጉባኤን መርቀዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በሚቆየው ኤግዚቢሽን በጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የፌደራል ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በተጨማሪም አሥራ ሁለት ተቋማትን ከ27 አገልግሎቶቻቸው ጋር በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን በአፍሪካ ቀዳሚ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያን በይፋ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በመድረኩ ላይ የሁለቱ ምክር ቤተች አፈ ጉባኤዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥትና የአገልግሎት አስተዳደር ዘመናትን ቢቆጠርም ዕድገት ከማፋጠን አኳያ ክፍተቶች ነበሩበት ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡ የወለደው የመደመር መንግሥትም የሲቪል ሰርቪስ የአገልግሎት ለውጥን በማያመጣና ዕድገትን በማያፋጥን ማነቆ የተተበተበ መሆኑን በግልፅ መገንዘቡን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደረሰው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ በገፅ 129 ላይ ከለውጡ በፊት የተደረጉ ሪፎርሞች የሀገራዊ ልማት ላይ ያለመመስረት እና በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ለድክመት የተጋለጡ መሆናቸውን በግልፅ መመላከቱን አስረድተዋል።

በዚህም የመደመር መንግሥት የተቋማትን ልዩ ባህሪና የሴክተሮችን ፍላጎት ታሳቢ በማድግ ጠንካራ ሥርዓት መገንባት የሚያስችል ሀገር በቀል የሪፎርም እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያን የሲቪል ሰርቪስ የአገልግሎት ምኅዳር ለማዘመን የተከናወኑ የሪፎርም እርምጃዎችም በዝግጅ፣ በትግበራና በማፅናት ምዕራፍ የሚያልፉበትን ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የተገልጋዮችን ቅሬታ መፍትሔ በመስጠት ቀልጣፋ የአገልግሎት አቅም እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቀማትም በመደመር መንግሥት መርህ የዜጎችን የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፋና የሚያዘምን ምኅዳር በመገንባት የተገኘውን ስኬት ማጎልበት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም ለማህበረሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማሰናሰል የአገልግሎት ደረጃን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

በቀጣይም ሲቪል ሰርቪሱን የበለጠ ለማዘመን የአመራሩን ቁርጠኝነትና የትውልድን ትጋት የሚሻ ወሳኝ ሀገራዊ የልማት አጀንዳ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም