ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዘመናዊ የአገልግሎት ምኅዳር የመንግሥትና ሕዝብን አመኔታ የሚያጎለብት አቅም እየገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዘመናዊ የአገልግሎት ምኅዳር የመንግሥትና ሕዝብን አመኔታ የሚያጎለብት አቅም እየገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ''ዲጂታል ለልህቀት'' በሚል መሪ ሐሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን፣ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ የሪፎርም ውጤቶችን የሚያሳየውን ኤግዚቢሽንና ጉባኤ መርቀዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በሚቆየው ኤግዚቢሽን፤ በጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የፌደራል ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በተጨማሪም አሥራ ሁለት ተቋማትን ከ27 አገልግሎቶቻቸው ጋር በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያን በይፋ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በፓናል ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን የአፍሪካና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና አስተዳደር አብዮት ተሞክሮዎችን መቀመር ተችሏል።

ይህም የኢትዮጵያን የመንግሥት አገልግሎቶች ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ዘመናዊ የፖሊሲና ፕሮግራም፣ አዋጅና ደንብ፣ መመሪያና ስታንዳርድ መቅረፅ የሚያስችል ሪፎርም ማካሄድ እንዳስቻለ ገልጸዋል። 

በዚህም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ የፈጠረው ምኅዳር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከብቁ የሰው ኃይል በማሰናሰል ፍሬያማ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ቴክኖሎጂን ከብቁ የሰው ኃይል ያቀናጀ ቁርጠኛ አገልግሎት ይፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎትም ከቴክኖሎጂ ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የአገልግሎት ምኅዳር በመፍጠር የመንግሥትና ሕዝብን አመኔታ እያጎለበተ መሆኑን ገልጸዋል። 

የተገልጋዮችን እርካታ የሚያሳድግ ምኅዳር ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመሶብ አንድ ማዕከል የዲጂታል አገልግሎትም የተገልጋዮችን እንግልት በመቀነስ ረገድ ጉልህ ፋይዳ እያስገኘ ነው ብለዋል።

 

የፌደራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ዓለማየው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት የተገልጋዮችን እንግልት በመቅረፍ የአገልግሎት እርካታን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ በተደረገው ውጤታማ የሪፎርም እርምጃም ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ 70 የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለ ገልጸዋል። 

መሶብ ወደ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ ተሸጋግሯል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በቀጣይም ሁሉንም የመንግሥት አገልግሎቶች በመሶብ የአንድ ማዕከል ለማካተት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተቋማት ሪፎርም ዋና ዳይሬክተር አሰፋ በየነ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ሪፎርም አገልግሎትን በማዘመን የአገልግሎት ጥራትን የሚያሳደግ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የሪፎርሙን ዘላቂነትና ውጤታማነት ለማሳደግ የአመራር ቁርጠኝነትና የቴክኖሎጂ ትግበራ ቀጣይነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል። 

በቀጣይም የተቋማት አቅም ግንባታን በማጠናከር፣ የሰው ኃይልና ትውልድን ከቴክኖሎጂ ጋር የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መክረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም