ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደረገ የልማት ስራዎች እያከናወነ ነው

አሶሳ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦የክልሉ መንግስት ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደረገ የልማት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ተናገሩ።

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በክልሉ ኡራ ወረዳ የስደተኞች ጣቢያ ተከብሯል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ‎ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ክልሉ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ከመቀበል ባለፈ ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።


 

በክልሉ አራት መጠለያ ጣቢያዎች ላይ  ከ112 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ ገልፀው ፥ ስደተኞች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ጠንካራ መስተጋብር በመፍጠር በአብሮነት እየኖሩ ነው ብለዋል።

‎ስደተኞች የውሃ፣ የትምህርት የጤናና ሌሎች የመሠረተ ልማቶችን ከተቀባዩ ማህበረሰብ እኩል ተጠቃሚ መሆናቸው የኢትዮጵያን ስደተኞች አያያዝ የተሻለ ተሞክሮ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር  ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ አመቺ መሆኗ በትልልቅ ዓለምአቀፍ ተቋማት ጭምር ዕውቅና ማግኘቷን ጠቅሰዋል።

‎ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ሲከበርም በመላው ዓለም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ስደተኞችን እውቅና ለመስጠት እና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ አስታውቀዋል።

‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትና ሕዝብ ለስደተኞች የኢኮኖሚ ዕድሎችን በመክፈት ያሳየው ምላሽ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።


 

በክልሉ በሚገኙ ስደተኞች የክልሉ መንግስት እና ማህበረሰብ እያደረጉት ያለው ሰብአዊ ድጋፍ እና የሚስተዋለው ማህበራዊ መስተጋብር የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሃም ሳሊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም