ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ዘርፍ የተያዙ የለውጥ ስራዎችን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል

ሃዋሳ ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ዘርፍ የተያዙ የለውጥ ስራዎችን በማገዝ ረገድ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ አመታዊ የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ ጉድኝት፣ የአጋርነትና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።


 

በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፣ በትምህርቱ ዘርፍ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የሚቀርፉ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባላቸው የሰው ሃይል፣ ግብአት፣ የአካባቢ ጸጋና ሌሎች ጉዳዮች በተልእኮና በትኩረት አቅጣጫ የመለየት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተልእኮና አቅጣጫን መሰረት ያደረጉ የምርምር ስራዎችና የትምህርት ፕሮግራሞችን በመቅረጽ በትምህርት ዘርፉ ለተያዙ የለውጥ ስራዎች ስኬት መስራት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም ገበያን መሰረት ያደረጉ ፕሮግራሞችን በጥናት ለይተው መቅረጽና የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ የምርምር ስራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የምርምር ተልእኮ የተሰጠው የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅም በመማር ማስተማር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና በምርምር ዘርፍ ያከናወናቸው ተስፋ ሰጪ ተግባራት ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰራዊት ሃንዲሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምርምሮች የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱና የኢንደስትሪዎችን ምርታማነት እንዲጨምሩ በትብብርና በትስስር እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጊዜውን የዋጁና እንደሀገር ያለውን ለውጥ የሚያስቀጥሉ የምርምር ስራዎችን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞችን ቀርጸው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የተቀረጹ የለውጥ ስራዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ አላማ ኮሌጁ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎቱ ባከናወናቸው ተግባራትና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተሞክሮ መለዋወጥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፍጮ ናቸው።


 

በዚህም ባለፉት አመታት ከአጋርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግር ፈቺ የምርምር ግኝቶች ላይ ፕሮጀክት በመቅረጽ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው ብለዋል።

በትምህርትና ስልጠና ዘርፍም ምርምርን መሰረት ያደረጉ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የፖሊሲ ውይይቶችና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ በትምህርቱ ዘርፍ የተደረጉ የለውጥ ስራዎችን ጨምሮ በትምህርት፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ አጋርና ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም