ቀጥታ፡

ከ60 ኮርሶች 47ቱን 'A+' ያስመዘገበችው ባለብሩህ ተስፋዋ ባለዋንጫ መሃንዲስ ሩት አባተ

ዛሬ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ASTU) ካስመረቃቸው 1 ሺህ 387 ተማሪዎች መካከል፣ የአንድ ሴት እጩ የመጪው ዘመን መሃንዲስ ስም በልዩ ክብርና በታላቅ ጭብጨባ አዳራሹን አናውጦታል። ይህ ስም የሩት አባተ ነው። ሩት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ያስመዘገበችው እጅግ አስደናቂ ውጤት የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ አድርጓታል።

የኤሌክትሪካል ፓወር ኤንድ ኮንትሮል ኢንጅነሪንግ (Electrical Power and Control Engineering) ተማሪዋ ሩት አባተ፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ከወሰደቻቸው 60 ኮርሶች መካከል 47ቱን 'A+' እንዲሁም የቀሩትን 13 ኮርሶች 'A' በማምጣት ሙሉ 4.00 (አራት ነጥብ) ውጤት አምጥታለች።

በዚህም በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ (Very Great Distinction) በመመረቅ የዓመቱ ኮከብ ተማሪ መሆን ችላለች።


 

ተወልዳ ባደገችባት አዳማ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቀችው ሩት፣ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት የበቃችው ከቅድመ መደበኛ መሰረቷ ጀምሮ ባደረገችው ተከታታይ ጥረት መሆኑን ትገልጻለች።

“የአዳማ ልጅ ነኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፤ ሁሌም የደረጃ ተማሪ ነበርኩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በትጋት እያጠናሁና እየሰራሁ ስለመጣሁ አቅሜን እያዳበርኩ እዚህ መድረስ ችያለሁ።

ዩኒቨርሲቲ ስገባም ከመጀመሪያ ዓመት ጀምሮ ለትምህርቴ ልዩ ትኩረት በመስጠትና ራሴን ለፈተናዎች በአግባቡ በማዘጋጀቴ የላቀ ውጤት አምጥቻለሁ፤ ለዚህም ፈጣሪን አመሰግናለሁ” ስትል ሩት የስኬቷን ሚስጥር ታጋራለች።

ይህን ታላቅ ውጤት ስታስመዘግብ ሁሌም አብረዋት የነበሩትን የቤተሰቦቿን ውለታ በኩራት ታነሳለች። ምንም ዓይነት ትኩረቷን የሚሰርቅ ነገር እንዳይገጥማት ቤተሰቦቿ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዳደረጉላት ትናገራለች።

“ቤተሰቦቼ ሁሌም ከጎኔ ሆነው እንድበረታ አድርገውኛል።

ምንም ነገር ከትምህርቴ እንዳያዘናጋኝ በመምከርና በመደገፍ አብረውኝ የስኬቴ ተጋሪ ሆነዋል። እኔም ጥረታቸውን ከንቱ አላደረግኩም፤ አላሳፈርኳቸውም" ስትል በምስጋና ትገልጻለች።

ሴቶች የትኛውንም ማህበራዊና አካባቢያዊ ጫናዎች አልፈው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ የምትመሰክረው ሩት፣ ይህ ውጤቷ ለሌሎች እህቶቿ ትልቅ ማበረታቻና አርአያ እንደሚሆን ታምናለች።


 

“እኛ ሴቶች የማንበብና የመማር ዕድል ካገኘን፣ የትኛውንም ዓይነት ማኅበራዊና አካባቢያዊ ጫናዎች አልፈን ለላቀ ስኬት መብቃት እንችላለን።

እኔም በቀጣይ የስኬታማ ሴቶች ህያው ምሳሌ ለመሆን ጠንክሬ እሰራለሁ።” ሩት በዚህ አሸናፊነቷ ብቻ ለመቆም አላሰበችም።

በቀጣይም በትምህርቷ ላይ ይበልጥ በመበርታት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የመቀጠል እቅድ አላት።

ከሁሉም በላይ ግን የተማረችውን ትምህርት ለሀገሯ በተግባር ማዋል ትልቁ ህልሟ መሆኑን ትናገራለች።

"በኢነርጂውና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለሀገሬ ጠቃሚና ችግር ፈቺ ባለሙያ ለመሆን እተጋለሁ" ስትል ጽኑ ምኞቷን ገልጻለች። ወጣቷ ባለዋንጫ መሃንዲስ ለዚህ ማዕረግ እንድትበቃ የረዷትን ፈጣሪዋን፣ ወላጆቿን፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራኖቿንና ጓደኞቿን አመስግናለች።

ይህ የሩት ታሪክ የራሷ የትጋት ብቻ ሳይሆን የወላጆች የዕለት ተዕለት ክትትልና የጋራ ጥረት ውጤት ጭምር መሆኑን የእናቷ ምስክርነት ያረጋግጣል።

የሩት እናት ወይዘሮ አዜብ ሻውል፣ የመጀመሪያ ልጃቸው የዋንጫ ተሸላሚ ሆና መመረቋ በቤተሰቡ ውስጥ ልዩ ደስታና ኩራት መፍጠሩን ይናገራሉ።

“ሩት እድገቷ ከንባብ ተለይቶ አያውቅም፤ እጅግ ጥሩ ስነምግባር ያላት ልጅ ናት። ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ሁሌም አንደኛ እየወጣች ነው እዚህ የደረሰችው" በማለት እናቷ የልጃቸውን የልጅነት ትጋት ያስታውሳሉ።

በዩኒቨርሲቲም ቆይታዋ ሁልጊዜ ተሸላሚ መሆኗን በኩራት ያነሳሉ።

እናቷ አያይዘውም፣ የሩት አባት ሁሌም የቅርብ አማካሪና አስጠኝ በመሆን ለዚህ ውጤት ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቅሰው፤ “ሩት ሀገሯን የምትጠቅም ልጅ ናት፤ ወደፊትም ከዚህ በላይ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ እመኛለሁ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም