ቀጥታ፡

አዲስ አበባን ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦አዲስ አበባን ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር ገለጹ፡፡

36ኛው የአፍሪካ ሕፃናት ቀን “ደህንነቱ እና ንጽህናው የተጠበቀ አካባቢ ለሁሉም ህጻናት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በአራዳ ፓርክ በልዩ ልዩ ሁነቶች ተከብሯል።


 

የከተማ አስተዳደሩ አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሕፃናት ላይ የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ኢንቨስትመንት ጠንካራ የሀገር መሰረት ነው፡፡

አዲስ አበባን ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ስራ ላይ መዋሉን አንስተው፣ በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ሕፃናት እና እናቶች የዚህ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተቋቋሙት የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት እናቶች የልጆቻቸውን ዕድገት በቅርበት እየተከታተሉ የሥራ ኃላፊነታቸውን ያለስጋት እንዲወጡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችና ሌሎችም ለሕፃናት ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ሕፃናት ቀን መከበሩ የከተማ አስተዳደሩ ለሕፃናት ያለውን ብሩህ ተስፋ የሚያሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመዲናዋ አራዳ ፓርክን ጨምሮ ለሕፃናት ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡

የተሰሩ የልማት ስራዎች የሕፃናትን አካላዊና አእምሯዊ ዕድገት ከማገዝ ባለፈ፣ ከተማዋ የተሞክሮ ማዕከል እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል፡፡


 

ቀኑ “ደህንነቱና ንጽህናው የተጠበቀ አካባቢ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ ሐሳብ መከበሩ ለሕፃናት ልዩ ትርጉም መሰጠቱን ያሳያል ያለችው ደግሞ የአዲስ አበባ ሕፃናት ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ሕፃን እድላዊት ኃይሌ ናት ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም