መንግስት ለስፖርት ዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለስፖርት ዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ለስፖርት ዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በስፖርት ልማት ዘርፍ ዙሪያ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተለያዩ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ በዚሁ ወቅት፤ የስፖርት ዘርፍ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ማድረግ አስችሏል ብለዋል፡፡
በአካልና የአእምሮ ብቁ የሆነ ትውልድን በመቅረጽና በመገንባት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቁመው ይህንን ድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
ዘርፉን ዘመኑን በዋጀ አሰራርና ሕግ ለመምራት የፖሊሲና የአዋጅ ማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፤ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረትና በገባው ቃል መሰረት በተሰሩ የተቀናጁ ተግባራት አመርቂ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተለይም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ በስፖርት ዘርፍ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታና በሌሎችም የስፖርት ወርቃማ ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ ከ45 ሺህ በላይ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው ለሕዝቡ ክፍት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የተገነቡት መሰረተ ልማቶች ሀገሪቱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮችን በብቃት እንድታስተናግድ ትልቅ አቅም መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በስፖርት ልማትና በስፖርት ዲፕሎማሲ ዘርፍ የተጀመሩ ስኬታማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።