ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ርዕይ በሁሉም መስክ እየሰመረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ርዕይ በሁሉም መስክ እየሰመረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ርዕይ በሁሉም መስክ እየሰመረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ''ዲጂታል ለልህቀት'' በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ የሪፎርም ውጤቶችን የሚያሳየውን ኤግዚቢሽን መርቀው ከፍተዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በሚቆየው ኤግዚቢሽን በጋዝና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የፌደራል ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በተጨማሪም አሥራ ሁለት ተቋማትን ከ27 አገልግሎቶቻቸው ጋር በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን በአፍሪካ ቀዳሚ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያን በይፋ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክትም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋማትን አገልግሎቶች ለማዘመን ከፍተኛ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቅሰዋል፡፡
የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማዘመን የተወሰዱ ስኬታማ የሪፎርም ሥራዎችም ለኢትዮጵያ የኩራት ምንጭ በመሆን በቴክኖሎጂ የሚመራና ዓላማ ተኮር ኢንቨስትመንት እንደሚያስገኙ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ቁልፍ የመንግሥት ተቋም ተቀይሮና ዘምኖ ማየትም ደስታን ይፈጥራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ወሳኝ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ነው ብለዋል።
ይህ ስኬት ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ትልሞች ምኞት ብቻ ሳይሆኑ፣ በራሳችን እጆችና አቅም የምንገነባቸው እውነታዎች መሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ ምስክር ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የባንክ ኢንዱስትሪ አገልግሎትና ምርታማነት በማዘመን ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ስኬትም በማጠናከር፣ ልምድና ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች በማካፈል እንዲሁም ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶች ማሻሻያ ከመሶብ አንድ ማዕከል ወደ ተንቀሳቃሽ በመቀጠልም ወደ ሞባይል መተግበሪያ ያደረገው ፈጣን ሽግግር በአስደናቂ ፍጥነት የታጀበ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ደረጃ ልክ እንደ መሶብ ሁሉም አገልግሎት በተቀናጀ ሥርዓት የሚሰጥበት የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ ብላ የጀመረችው የመሶብ አገልግሎት አሁን ላይ 70 ደርሷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ልምድ የወሰደችባቸው ሀገራት በአሥር ዓመታት ውስጥ ሰባ እንዳልደረሱ በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትም በአስደናቂ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።
የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያው በአፍሪካ በሁሉም መስክ የመጀመሪያው የተቀናጀ የአገልግሎት መተግበሪያ ነው ብለዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል መገልገል አስደናቂ ሆኖ ሳለ፤ ዜጎች በእጅ ስልካቸው ጉዳያቸውን ባሉበት ቦታና በየትኛውም ጊዜ መገልገል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የመሶብ አገልግሎትም የመንግሥት አገልግሎትን ከአንድ ማዕከል ወደ ተንቀሳቃሽ፣ ከተንቀሳቃሽ ወደ የእጅ ስልክ ያሸጋገረና ጥቂት ሀገራት ብቻ የደረሱበት ስኬታማ ሥራ መሆኑን አንስተዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ በብዙ ጉዳዮች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተምሳሌት የሚያደርጋት መሆኑን ጠቅሰው ብልፅግናን ለማረጋገጥ የበለጠ ትጋት የበለጠ ሥራ እና ልፋት እንደሚጠይቅም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ እንዲሆኑ፣ ለልጆቿ ድህነትን የማታወርስ አገር መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ርዕይ በሁሉም መስክ እየሰመረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡