ቀጥታ፡

የትውልዱ የሉዓላዊነት አጀንዳ ሀገርን በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ማድረግ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የወደፊቱ የዓለም ውድድርና የፉክክር ምንጭ የተፈጥሮ ሀብት ሳይሆን ዕውቀት፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ መሆኑን በመገንዘብ አዲሱ ትውልድ ሀገርን በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ጥሪ አቀረቡ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 387 ተማሪዎች አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በአሁኑ ወቅት ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂና ታዳሽ ኃይል ዓለምን በፍጥነት እየቀየሩት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ብልጽግና ለማሸጋገርም የሰው ሀብትን ማልማትና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎችን በልዩ ሁኔታ ማበረታታት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ግንባታ ጠንካራ መሠረት እየጣለ መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተሠሩ የኤአይ እና የመድኃኒት ቅመማ የፈጠራ ሥራዎችና የምርምር ውጤቶችን ይበልጥ በማጠናከር ወደ ገበያ ለማስገባት ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ተመራቂዎች ዛሬ ያገኙት ዲግሪ የእውቀት ጉዞ አንድ ምዕራፍ መጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ መዳረሻ አለመሆኑን ገልጸው፤ በሕብረተሰብ ውስጥ እውነተኛ ስኬታማ የሚባሉት ሰዎች ሁልጊዜም ለመማር ዝግጁ የሆኑና ራሳቸውን የሚያሻሽሉ ብቻ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

“ሀገራችሁ ከእናንተ የምትጠብቀው ሥራ ፈጣሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አበልጻጊዎች፣ ችግር ፈቺዎችና በሥነ-ምግባር የታነጹ መሪዎች እንድትሆኑ ነው” ብለዋል።

ቀደምት አባቶችና እናቶች ሀገርን በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ሉዓላዊነቷን ጠብቀው እንዳቆዩ ሁሉ፣ የዚህ ትውልድ የሉዓላዊነት አጀንዳ ደግሞ ሀገርን በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።

ተመራቂዎች ኢትዮጵያን በዕውቀትና በጥበብ ከፍ ለማድረግ በርትተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው የመማር-ማስተማርና የምርምር ጥራትን ለማረጋገጥ በመምህራን ብቃት፣ ፕሮግራሞቹ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፥ የመጨረሻ ውሳኔ ከትምህርት ሚኒስቴር እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመሠረተ-ልማት ረገድ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተው፤ አምስት የልህቀት ማዕከላትንና 40 ስፔሻላይዝድ ቤተ-ሙከራዎችን የሚይዝ የምርምር ፓርክ ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች በቀጥታ ወደ ሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉ ለማስቻል የሥራ ዝግጁነትና የፈጠራ ክህሎት ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም