የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጉዞ የሚሳካው በወጣት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ቁጭት፣ ትጋትና ፈጠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጉዞ የሚሳካው በወጣት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ቁጭት፣ ትጋትና ፈጠራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጉዞ የሚሳካው በወጣት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ቁጭት፣ ትጋትና ፈጠራ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የ2018 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎቹን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ተመራቂዎች የሀገሪቱን የዲጂታል ሽግግርና የልማት ጉዞ መምራት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
የትምህርት ሥርዓቱ ከነባር ዕውቀቶች ተነሥቶ ዛሬ ላይ በኦንላይን ትምህርት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተደገፈበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፥ አሁን ያለው ትውልድም የዚህ ፈጣን የለውጥ ዘመን ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካትም ዕውቀት ማመንጨት፣ ቴክኖሎጂ ማልማትና ኢንዱስትሪ መገንባት የሚችሉ ሀገር ወዳድ ወጣት ባለሙያዎች ማፍራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
መንግሥት በቀረጸው የትምህርት ፖሊሲ በመታገዝ ብቃት ያለውና ምርታማ የሰው ኃይል ለመገንባት በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እንደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማት ትውልድን በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነ ምግባር በማነጽ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የትናንትናዋ ኢትዮጵያ የምትችለውን ሠርታለች፤ ከዚህ በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ ደግሞ በእናንተ ትከሻ ላይ ቆማለች ሲሉም ነው ለተመራቂዎቹ በአፅንኦት የተናገሩት።
የዛሬ ተመራቂዎችም በቁጭት በመመራመርና ቴክኖሎጂ በመፍጠር ኢትዮጵያን ታላቅና የበለጸገች ሀገር ማድረግ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል።
ወጣቶች ትኩረታቸውን ከሚሰርቁ አሉታዊ አጀንዳዎች ርቀው በቁጭት በመነሣት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲፈጥሩና ሀገራቸውን እንዲቀይሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ወደ ተግባር በገባበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት የሀገርና የዓለምን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ ባለ ራዕይ ተመራማሪዎችና ሥራ ፈጣሪዎች መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተዋል።
መንግሥት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችንና ተመራቂዎችን በዘርፉ በሚፈጠሩ የሥራ ቦታዎች አወዳድሮ በማሠማራት፣ ሥራ ፈጣሪዎችንና ተመራማሪዎችን በማበረታት በፖሊሲ፣ በሕግና በአሠራር እንደሚደግፍም ገልጸዋል።
እንደ ዲጂታል መታወቂያ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓቶች እንዲሁም ሰው ሠራሽ አስተውሎት መስፋፋታቸው የመንግሥትን ዐቅምና ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዕውቀትና በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራትና ለነገዎቹ የኢትዮጵያ ተስፋዎች ስኬት ያልተቆጠበ ድጋፍ ለሰጡ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ መምህራንና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሀገር ታመሰግናችኋለች ብለዋል።