ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃትና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃትና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ፡፡   

ኢትዮጵያ በብዝኃ ኢኮኖሚ መርህ ላይ በመመስረት በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፎች ሰፊ እምርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች። 

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ረገድ ወደ ላቀ ምዕራፍ ላይ እንድትደርስና በዘርፉ የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ ታስቦ የተወጠነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በስኬት ተካሂዷል። 

በዚህም የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳዩ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎችም ቀርበው በስኬታማነት ተከናውኗል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ባለፉት ዓመታት ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ 

ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግና መዋቅራዊ ሽግግርን በማምጣት ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ጠንካራ መሠረት መጣሉንም ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፤ የገቢ ንግድን በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻሉን እንዲሁም የባለሀብቱን ተሳትፎና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ረገድ ትልልቅ ስኬቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መዋቅራዊ ሽግግሩ በፈጣን ሁኔታ ለውጥ በማሳየት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ 

ግንዛቤን በማስጨበጥ፣ ቀጣይነት ያለውና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ በማድረግ እንዲሁም የኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ጎልቶ እንዲታይ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው የማምረት አቅምና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሰው የኢንዱስትሪው አጠቃላይ የማምረት አቅም አጠቃቀም 66 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። 

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም  ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

በተደረጉት መዋቅራዊ ለውጦች ምክንያት በሁሉም ዘርፍ የተሻሉ ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን ጠቅሰው ዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ይዞ ከመምጣቱም በላይ ለሀገራዊ ብልጽግና መረጋገጥ ትልቅ አቅም እየሆነ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም