የጭናና አካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን በንቃት በመጠበቅ የወትሮ ጀግንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የጭናና አካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን በንቃት በመጠበቅ የወትሮ ጀግንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የጭናና አካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን በንቃት በመጠበቅ የወትሮ ጀግንነቱን የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የመከላከያ መገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሠረት ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊት 403ኛ መከታ ኮር የተመሠረተበትን 4ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ ይገኛል።
ኮሩ በታሪካዊቷ ጭና ቀበሌ ያስገነባውን የጭና ሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ አስመርቋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፣ የ403ኛ መከታ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ እና ሌሎችም የጦር መኮንኖች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ይህ ጤና ጣቢያ በወርሃ ነሐሴ 2013 ዓ.ም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በጭና ቀበሌና አካባቢው የሀገርን ክብርና አንድነት ለማስጠበቅ በጀግንነት ለተዋደቁ የሠራዊት አባላት፣ የጸጥታ ኃይሎችና ሲቪል ማኅበረሰቦች ዘላቂ መታሰቢያ እንዲሆን የተገነባ ነው።
ጤና ጣቢያው ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከ10 በላይ የጤና አገልግሎት ዓይነቶችን የሚሰጥ ሲሆን ለአካባቢው ነዋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እንግልትን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
በቀድሞው ሕወኃት የጥፋት ቡድን በግፍ ለተጨፈጨፉ ንጹኃንና ሀገር ለማዳን ለተሰው የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ቋሚ መታሰቢያ ሙዚየም ሆኖ ያገለግላል።
የመከላከያ መገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሠረት በምረቃው ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የዳባትና ደባርቅ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የጥፋት ቡድኑን በመመከት ሀገርን ከመፍረስ የታደገ ጀግና መሆኑን አውስተዋል።
የቀድሞው የሕወኃት አንጃ ሀገር የማፍረስ ሕልሙን ሰንቆ 10 እግረኛና አንድ ኮማንዶ ክፍለ ጦሮችን በማሰለፍ ቢመጣም፤ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት፣ በተለያዩ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በሀገር ወዳዱ የዳባትና ደባርቅ ሕዝብ ትብብር ጭና ላይ ሕልሙ ጉም ሆኖ መቅረቱን ገልጸዋል።
በወቅቱ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ የሰጠውን የፅሞና ጊዜ ተጠቅሞ ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ ቢሞክርም፤ ዛሬም በጀግንነት ማሸነፍ የባሕርይ መገለጫቸው የሆነው የመከላከያ ሠራዊት የጠላትን ቅስም ሰብሮ መመለሱን አረጋግጠዋል።
የ403ኛ መከታ ኮር እንደ 72ኛ ጭና፣ 71ኛ ቃኘው እና በሰል ድል አብሳሪ ክፍለ ጦሮች ሁሉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጀግንነት ከመጠበቅ ባለፈ፣ የሕዝብ አለኝታነቱን በማኅበራዊ ኃላፊነቱ ጭምር ማሳየቱን ገልጸዋል።
ይህ የሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ የተሰውና በግፍ የተገደሉ ጀግኖች ማስታወሻ፣ ቤተሰቦቻቸው ደግሞ እረፍት ያገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሩ አባላት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ኅብረተሰቡን አስተባብረው የገነቡት በመሆኑ ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልጸው፤ መንግሥት ምንጊዜም ሰላም እንደሚፈልግና የአካባቢው ማኅበረሰብም ሰላሙን በንቃት በመጠበቅ የወትሮ ጀግንነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የ403ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን በበኩላቸው፤ ኮሩ ኢትዮጵያን ከጥፋት እንዲሁም ሕዝብን ከብተና የታደገ ታላቅ መስዋዕትነት መክፈሉን ገልጸዋል።
የጭና የሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያም ለሀገራቸው ሲሉ ግፍን ለተቀበሉና ውድ ሕይወታቸውን ለገበሩ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላትና የፀጥታ ኃይሎች የቆመ የዘላለም መታሰቢያ መሆኑን አስገንዝበዋል።