በወላይታ ዞን በዘንድሮ መኸር እርሻ ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን በዘንድሮ መኸር እርሻ ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል
ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ132 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ (ዶ/ር)ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው መኸር እርሻ 132 ሺህ 776 ሄክታር መሬት በአዝዕርትና በሆርቲካልቸር ሰብሎች ይለማል።
ከሚለማው መሬትም ከ19 ሚሊዮን 96 ሺህ 767 ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመኸር ወቅት የግብርና ልማቱን ውጤታማ ለማድረግና ምርታማነትን ለማሳደግም 112 ሺህ 979 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
በዞኑ ከሚለማው መሬት አብዛኛው በሜካናይዜሽን የሚታረስና በኩታ ገጠም የሚለማ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አርሶ አደሮች በጋራ አልምተው ውጤታማ እንዲሆኑ መምሪያው ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ የባለሙያ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳሞት ዋጃ ቀበሌ አርሶ አደሮች ፤ በመኸር እርሻ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ማሳቸውን እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ባለሙያዎችም የሙያ ምክር ከመስጠት ጀምሮ በተለያየ መንገድ እያገዟቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የዋጃ ቀሮ ቀበሌ አርሶ አደር ወይዘሮ ቆንጂት ዋትሮ በበኩላቸው፤ ማሳቸውን በተደጋጋሚ በማረስ ለዘር ዝግጁ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።