በዞኑ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የጎርፍ መከላከያ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የጎርፍ መከላከያ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው
ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የጎርፍ መከላከያ ስራዎች በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የተጠሪ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክረምትን ተከትሎ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን በጥናት በመለየት የመከላከል ተግባሩ በቅንጅት እየተከናወነ ነው።
በጥናቱም የአባይ ሸለቆን ተከትሎ የሚገኙ ወረዳዎች ለክረምት ጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በመሆናቸው አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ የጎርፍ መከላከያ ስራዎች በመስራት የህዝብ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለማስቀረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጋላጭነት በተለዩ የሸበል በረንታ፣ እንብሴ ሳርምድር፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ፣ ደጀን፣ ባሶ ሊበን፣ ስናንና የአዋበል ወረዳዎች መሆኑን አስረድተዋል።
እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ በሚሰራው የጎርፍ መከላከል ስራ ከ55 ሺህ በላይ ሰዎችን ለመታደግ ታልሞ እየተከናወነ መሆኑ አመልክተዋል።
በጎርፍ መከላከያ ስራዎቹም ከ46 ኪሎ ሜትር በላይ ጎርፍ መቀልበሻ ቦይ፣ 6 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የእርከን ስራ፣ ከ110 ሺህ ሜትር በላይ የማፋሰሻ ቦይ ግንባታና ክትር መሰራቱን ገልጸዋል።
ለጎርፍ መከላከያ ስራዎቹ ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዞኑ የአዋበል ወረዳ የጀር ገብርኤል ቀበሌ ነዋሪ አቶ የቆየ ደጉ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋን መከላከል ስራ ባለመሰራቱ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ ሰብላቸውን ከጥቅም ውጭ ያደርግባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመቋቋም በባለሙያዎች ምክረ ሃሳብና ድጋፍ በመታገዝ የእርከን፣ የጎርፍ መከላከል ስራ መስራታቸውን አስረድተዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አንችናሉ ደሱ በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት በጎርፍ ምክንያት የዘሩት የስንዴ ሰብል ከጥቅም ውጭ መሆኑን አውስተዋል።
ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከበጋው ጀምሮ እስካሁን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የጎርፍ መከላከያና መቀልበሻ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።