ቀጥታ፡

በሀዋሳ ከተማ ህብረተሰቡ ለልማት የሚያደርገው ተሳትፎ ለከተማዋ ፈጣን ዕድገት ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል 

ሀዋሳ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በሀዋሳ ከተማ በሕብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ፈጣን ዕድገት ተጨማሪ አቅም መፍጠራቸውን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት፤ የሀዋሳ ከተማን ዕድገት ለማሳለጥ ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመሠራቱ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።

የከተማዋን ዕድገት በማፋጠንም የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉንም ገልጸዋል።

በከተማዋ በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች አመራሩ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ባከናወናቸው ተግባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማዋን ለኑሮ ምቹ፣ ለቱሪስት መስህብ እና ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ተመራጭ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በልማት ሥራዎች ላይ ያሳዩትን ተነሳሽነትና ትብብር መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

"ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ከተማዋን ከፍ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች አሁንም እየተሰሩ ይገኛሉ፤ ይህንን አጋርነት ይበልጥ ለማስቀጠልም በቁርጠኝነት እንሠራለን" ብለዋል።

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የክልሉና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም