የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ አመራሩ ነባራዊ ሁኔታን በአግባቡ በመረዳት ጥረቱን ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ አመራሩ ነባራዊ ሁኔታን በአግባቡ በመረዳት ጥረቱን ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦የተለመደውን አሠራር በመከተል የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ ስለማይቻል አመራሩ ነባራዊ ሁኔታውን በአግባቡ በመረዳት ጥረቱን ማጠናከር አለበት ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል አመራሮች ቡድን የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ጎብኝቷል።
በዚሁ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የተለመደውን አሠራር በመከተል የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ ስለማይቻል የለውጥ አመራሩ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስቀድሞ በመረዳት ስትራቴጂዎች ቀርጾ መንቀሳቀስ አለበት።
የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንም በዚህ መነሻነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።
ገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዓላማን በማሳካት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የመሠረተ ልማት ዝግጅት ምዕራፍን በማለፍ ካፒታል፣ ምርታማነትና ከተሜነት የሚገናኙበትና የጋራ ፍሰታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑንም ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የንግድና ሎጂስቲክስ፣ ግብርና ምርት ማቀነባበር፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ አገልግሎትና ሌሎች ዘርፎች በዞኑ ወደ ሥራ ገብተዋልም ነው ያሉት።
በእነዚህ ሥራዎች ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን ጨምሮ የቻይና፣ የአሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የሆላንድ፣ የጣሊያንና የሌሎች አገራት ኢንቨስተሮች እንደሚገኙም አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን የሚያረጋግጡ እነዚህን ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች በማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ይበልጥ የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል።
በዚህ ጉብኝት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።