ቀጥታ፡

የመከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር በታሪካዊቷ ጭና ቀበሌ ያስገነባውን የጭና ሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ አስመረቀ

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር በታሪካዊቷ ጭና ቀበሌ ያስገነባውን የጭና ሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ አስመርቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የአስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር)፣የመከላከያ መገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሠረት፣ የ403ኛ መከታ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል አዘዘው መኮንን፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ እና ሌሎችም የጦር መኮንኖችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ጤና ጣቢያው በወርሃ ነሐሴ 2013 ዓ.ም በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌና አካባቢው የሀገርን ክብርና አንድነት ለማስጠበቅ በጀግንነት ለወደቁ የሰራዊት አባላት፣ የጸጥታ ኃይሎችና ሲቪል ማህበረሰቦች ዘላቂ መታሰቢያነት የተገነባ ነው።


 

የቀድሞው ሕወሓት በወቅቱ ሀገር የማፍረስ ሕልሙ ሲመክን በጭና ቀበሌ በፈጸመው ጥቃት ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣ ቤት የተቀመጡ አቅመ ደካሞችን፣ ሕፃናትና ወጣቶችን መግደሉ ይታወሳል።

የአካባቢውን እንስሳት በመግደል ሀብት እያቃጠለ የጭካኔ ጥጉን ማሳየቱ ነው የተገለጸው።

በዚያን ወቅት የሀገር መከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር የጥፋት ቡድኑን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ቅዠቱን አምክኗል።

በወቅቱ ሀገር ለማስጠበቅ ለተሰው ጀግኖች ኮሩ ዘላቂ መታሰቢያ ጤና ጣቢያ ገንብቶ ለማህበረሰቡ አስረክቧል።


 

የጭና ሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያ በሀገር መከላከያ ሰራዊት 403ኛ መከታ ኮር የገንዘብ መዋጮና ጉልበት የተገነባ ሲሆን፣ ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በጀግንነት ከማስከበር ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ ሕዝባዊ ሰራዊት መሆኑን በተግባር ያሳየበት ነው።

የሰማዕታት መታሰቢያ ጤና ጣቢያው ከ10 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያገለግል ሲሆን የተላያዩ  የጤና አገልግሎቶችን መስጠት ያስችላል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የነዋሪዎችን እንግልት ይቀንሳል ተብሏል።

ከዚህም ባለፈ በጥፋት ቡድኑ በግፍ የተጨፈጨፉ ንጹሃንና ሀገር ለማዳን ለተሰው የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ቋሚ መታሰቢያ ሙዚየም ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም