ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ የፅዳት ንቅናቄን አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ የፅዳት ንቅናቄን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ):- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የፅዳት ንቅናቄ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአንድ ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃ መለኪያው ፅዳቱ፣ ውበቱና አረንጓዴነቱ ነው ብለዋል።
ውብ፣ ፅዱና አረንጓዴ ከተማ ለመፍጠር ህዝባችንን እና ባለድርሻ አካላትን በቁርጠኝነት ማስተባበር ችለናል፤ በአፍሪካ ደረጃ ከ10ሩ ፅዱ ከተሞች አንዷ ለመሆን የበቃነውም በዚህ ታላቅ የህዝብ ተሳትፎና ውጤታማ ስራ ምክንያት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ቀደም ሲል በፅዳትና ውበት ጉድለት እንዲሁም በአረንጓዴ ሽፋን ማነስ ትወቀስ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህንን ገፅታ በተከናወኑ ተከታታይና የተቀናጁ ስራዎች መቀልበስ መቻሉን ተናግረዋል።
"ፅዳት የዘወትር ተግባርና ባህል መሆን አለበት" ያሉት ከንቲባዋ፤ ፅዳት ከእለት ተእለት ህይወታችንና ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ጋር የተሳሰረ መሆኑን በሁሉም አካባቢ ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፅዳት ከቤት እንደሚጀምር በመጠቆምም፣ እያንዳንዱ ነዋሪ በየአካባቢውና በየተቋማቱ ተግባሩን እንደ ባህል ሊያዘወትረው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ባህላችን እስኪሆን ድረስ ያለእረፍትና በትጋት መስራት፣ ሁልጊዜም ክትትል ማድረግና ሁላችንም የፅዳት አምባሳደር መሆን ይኖርብናል በማለት አደራ ብለዋል።