ቀጥታ፡

አዲስ አበባን ጽዱ ፣ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ ሕዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን አስገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦አዲስ አበባን ጽዱ ፣ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ ሕዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የጽዳት ንቅናቄ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።


 

በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የመዲናዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አዲስ አበባን ጽዱ፣ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ ሕዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል።

አዲስ አበባን በአፍሪካ ጽዱ ከሆኑ አሥር ከተሞች አንዷ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ ይሄንን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሕዝቡ ርብርብ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።


 

ጽዳት ከአካባቢ ውበት ባሻገር ለጤና መጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፣ ኅብረተሰቡ ጽዳትን ባህል ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

"ዛሬ በይፋ ያስጀመርነው የጽዳት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን በየብሎኩና በየአካባቢው የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

ደረጃውን የጠበቀ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለመዘርጋት የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም