በዓለም ዋንጫው ኮትዲቯር ከጀርመን የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ዋንጫው ኮትዲቯር ከጀርመን የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ አምስት መርሐ ግብር ኮትዲቯር ከጀርመን ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ታከናውናለች።
ጨዋታው ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ በቶሮንቶ ስታዲየም ይከናወናል።
የምዕራብ አፍሪካዋ ኮትዲቯር በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ኢኳዶርን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ይህም በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ድል የቀናት የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል።
የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ጀርመን በመጀመሪያ ጨዋታዋ ኩራሳኦን 7 ለ 1 ረምርማለች።
ጀርመን ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ብታገኝም ኮትዲቯር ጠንካራ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
አሸናፊ ቡድን ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል።
በዚሁ ምድብ ኢኳዶር ከኩራሳኦ በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በመጀመሪያ ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ሁለቱ ሀገራት ድል ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በተያያዘም የምድብ ስድስት ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ኔዘርላንድስ ከስዊድን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በሂውስተን ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በመጀመሪያ ጨዋታ ኔዘርላንድስ ከጃፓን ጋር ሁለት አቻ ስትለያይ ስዊድን ቱኒዚያን 5 ለ 1 አሸንፋለች።
ኔዘርላንድስ ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏን ለማስፋት ማሸነፍ ይጠበቅባታል።
ተጋጣሚዋ ስዊድን ካሸነፈች ወደ ጥሎ ማለፍ ትገባለች።
በዚሁ ምድብ ቱኒዚያ ከጃፓን ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ በሞንቴሬይ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በመጀመሪያ ጨዋታው ሽንፈት ያስተናገደችው ቱኒዚያ በውድድሩ ላይ ለመቆየት ጨዋታውን ማሸነፍ ግድ ይላታል።
አንድ ነጥብ ያላት ጃፓን ማሸነፍ ጥሎ ማለፍ የመግባት እድሏን ያሰፋላታል።