ቀጥታ፡

በክልሉ ከተሞችን ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ቡታጅራ ፤ ሰኔ 13/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞችን ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጨምር ኃይሌ፤ በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ሁሉን አቀፍ የሆነ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተሞቹ ልማት የአስፋልት መንገዶችን ጨምሮ፣ የእግረኞች እና የሳይክል መንገድ እንዲሁም ለመዝናኛ ምቹ የሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማካተት ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ቡታጅራ ከተማ በኮሪደር ልማትም ይሁን በወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት የምትጠቀስ መሆኗን አንስተው፣ በሌሎች የክልሉ ማዕከል ከተሞችም መቀጠሉን ተናግረዋል።

የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ከቡታጅራ በተጨማሪ በወራቤ ከተማም እየተሠራ መሆኑን አንስተው፣ በክልሉ ከተሞችን ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በሰባት የክልል ማዕከል ከተሞች 165 ኪሎ ሜትር ኮሪደር ልማት በሁለት ምዕራፍ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ መሆኑን አንስተው፣ አሁን ላይ 61 ኪሎ ሜትር ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅቷል ብለዋል።

በክልሉ የገጠር ኮሪደር ልማትን በልዩ ትኩረት በመሥራት የአርሶ አደሮችን አኗኗር ከማሻሻል ባለፈ ከከተሞች ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም