ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና የሊጉን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ከነገሌ አርሲ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/ 2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያገኛል።

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከነገሌ አርሲ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።

ሲዳማ ቡና በ64 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ነገሌ አርሲ በ56 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል የቀናው ሲዳማ ቡና በዛሬው መርሐ ግብር ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋግጣል።

በ35ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማን 2 ለ 1 ያሸነፈው ነገሌ አርሲ ዋንጫውን ለማንሳት ያለውን ጭላንጭል ተስፋ ለማስቀጠል የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል።

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በ17ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ነገሌ አርሲ ዳዊት ተፈራ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው መርሐ ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ምድረ ገነት ሽሬ በ37 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ49 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ምድረ ገነት ሽሬ ከወራጅ ቀጠና  ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ጨዋታውን ማሸነፍ ይኖርበታል።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ45 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ቡና በ46 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ35ኛ ሳምንት በአዳማ ከተማ የ2 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደው ንግድ ባንክ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።

ፋሲል ከነማ ከአርባምንጭ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

በ35ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 የረታው ፋሲል ከነማ በ49 ነጥብ ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አስመዝግቧል።

ጨዋታው ፋሲል ከነማ በድል ጉዞው ለመቀጠል አርባምንጭ ከተማ ከመውረድ ለመትረፍ እያደረገው ባለው ጉዞ ሶስት ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ነው።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት እስከ ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ናትናኤል ዳንኤል በተመሳሳይ 14 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።

የፋሲል ከነማው ታምራት እያሱ በ12 እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በ11 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም