ቀጥታ፡

በድህረ ምርጫው ወቅት ብሄራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና የወል ትርክትን ለማጠናከር እንሰራለን

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በድህረ ምርጫው ወቅት ብሄራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ፣ የህዝብን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም የወል ትርክትን ለማጠናከር በሚያስችሉ የይዘት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል።


 

የተቋሙ ሰራተኞች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ብሄራዊ ጥቅምን የሚያረጋግጡ፣ የልማት ተሳትፎን የሚያሳድጉ፣ የጋራ ትርክትን የሚያጸኑ የይዘት ውጤቶች ህብረተሰቡ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ሚና ይጫወታሉ።

በአሁኑ ወቅት ያለባቸውን ድርብ ኃላፊነት በመገንዘብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ፣ የሀገርን ሰላምና ልማት የሚያጸኑ፣ የጋራ ትርክትን የሚያጎለብቱ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢዜአ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ህዝቡ ለተሳተፈበት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውንነት አስቻይ ምሕዳር እንዲፈጠር ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉባቸው እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የታደሙበት የምርጫ ክርክር መድረኮች እንዲካሄዱ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የምርጫ ዘገባን በተመለከተም በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎችን በማከናወን፤ ፍትሐዊ፣ ነጻ፣ ተዓማኒና አሳታፊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ የይዘት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመው፣ መገናኛ ብዙሀን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የበኩላቸውን መወጣት የሚያስችላቸውን ስልጠናዊ ፓናል ማዘጋጀቱንም አስታውሰዋል።

በድኅረ ምርጫ ወቅትም ኢዜአ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያረጋግጡ፣ የጋራ ትርክትን የሚያጎለብቱ፣ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግናን የሚያጠናክሩ ዘገባዎችን በስፋት እንደሚሰራም አብራርተዋል።

ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጥራት ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ፣ ብሎም የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነት ለተቀረው ዓለም ማሳየት እንደሚገባም አብራርተዋል።


 

የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ የውይይት መነሻ ሐሳብ ባቀረቡበት ወቅት፤ ለሰባተኛው ምርጫ ስኬታማነት ኢዜአን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው ለመሳተፍ እንዲችሉና በካርዳቸው የሚፈልጉትን እንዲመርጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ይዘቶች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በድኅረ ምርጫ ወቅትም የተቋሙ ሠራተኞች አገራዊ ትብብርን የሚያጠናክሩና በጋራ መሥራትን የሚያበረታቱ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።


 

የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ በበኩላቸው፤ ሕብረተሰቡን ለሰላም፣ ለልማትና ዲሞክራሲ የበለጠ የሚያሰልፉ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል ብለዋል።

በምርጫ ዋዜማ ሲወጡ የነበሩ የተሳሳቱ መረጃዎችን መመከት የሚያስችሉ ሥራዎችን መገናኛ ብዙኃን መሥራታቸውን አመልክተው፤ ኢዜአም በተናበበ አግባብ ሀሰተኛ መረጃዎችን እያጣራ እውነታውን ሲያቀርብ እንደነበር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም