በክልሉ አጠቃላይ በቡና ከሚለማው መሬት ውስጥ 20 በመቶውን በመስኖና በኩታ ገጠም ለማልማት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አጠቃላይ በቡና ከሚለማው መሬት ውስጥ 20 በመቶውን በመስኖና በኩታ ገጠም ለማልማት ይሰራል
አዳማ፣ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ በቡና ከሚለማው መሬት ውስጥ 20 በመቶውን በመስኖና በኩታ ገጠም ለማልማት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የደረጃው የሚገኙ የቡና ልማት ባለሙያዎች፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የቡና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ አሠራርንና ሙያን ብቻ መሠረት ባደረገ መልኩ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ለዚህም ሲባል አዲስ የቡና ልማት ፓኬጅ ተቀርዖ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ፓኬጁ ከባለሀብቱና ከአርሶ አደሩ ማሳ እስከ ገበያ ያለውን የቡና እሴት ሰንሰለት የተከተሉ አዳዲስ አሠራሮችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚሁ መነሻነት በክልሉ ከሚለማው አጠቃላይ የቡና መሬት ውስጥ 20 በመቶው በመስኖና በኩታ ገጠም እንደሚለማም ኃላፊው ገልጸዋል።
ይህም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚመረተውን የቡና ምርት ወደ ሁለት ጊዜ ለማሳደግ መታቀዱን አስረድተው በሄክታር የሚገኘውን ምርት ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በተለይም የቡና ልማትን በመስኖ ለማከናወን በውሃ አጠቃቀም ላይ ሙያዊና ሳይንሳዊ የቡና ልማት ሥነ-ዘዴን መከተልና መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የቡና ልማት ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሠራተኞች አርሶ አደሩን በንቃት ባሳተፈ መልኩ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ከአርሶ አደሩ ማሳ እስከ ግብይት ድረስ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ጥራቱን ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ ወሳኝ ነውም ብለዋል።
በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የቡና ልማት ምርታማነትን ለመጨመርና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በብዛት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል የቡና ልማት በባህላዊ መንገድና በዘልማድ የሚከናወን በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ዘርፉ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ልዩ ትኩረት ይሰራልም ብለዋል።