ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ተሳትፎ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጡበት ነው

አዲስ አበባ፣ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያደረጉት ተሳትፎ ለጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጡበት ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር ገለጹ።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል።

በምርጫው ዕለት ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከማለዳው ጀምሮ በነቂስ በመውጣት ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን፤ የድምፅ አሰጣጥ ባልተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎችም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ምርጫው ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ የተጠናቀቁ የቆጠራ ውጤቶችን በየደረጃውና በየወቅቱ ለኅብረተሰቡ ይፋ እያደረገ ይገኛል።

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ተወካዮቻቸውና መሪዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መምረጣቸውን ገልጸዋል።

ይህም ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት ያሳየ ጠንካራ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

አምባሳደሯ አክለውም፤ ሕብረቱ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት መግለጫ በማውጣት ምስጋና ማቅረቡን አስታውቀዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግብዣ በተወሰኑ ጣቢያዎች ላይ ምልከታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን ለመስጠት በሰልፍ ቆመው ማየታቸውን እጅግ የሚያስደንቅ እንደነበር አስታውቀዋል።

ይህ የምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ውስጥ ትልቅ እና አስፈላጊ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውጥረት ባለበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ ኢትዮጵያ ምርጫ ማካሄዷ እና ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ተወካዮቹን መምረጥ መቻሉ ትልቅና ጠንካራ መልዕክት እንዳለው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም