ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት በመፍጠር ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት በመፍጠር ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት የሚያስችል እንደሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 23/2018 ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይፋዊ የሕዝብ ውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ቢራቱ ይገዙ የረቂቅ አዋጁን መነሻ ሐሳብ ባቀረቡበት ወቅት፤ አዋጁ የኢትዮጵያን ስታቲስቲክስ ሥርዓት ለማጠናከርና የበለጠ ለማዳበር፣ እንዲሁም ሥርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ዘመኑን የዋጀ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም የመረጃ ጥራትንና ተደራሽነትን በማሻሻል እንዲሁም ግልጽነትን በማረጋገጥ፣ መረጃው ተአማኒነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የሚቀርቡ መረጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነትን ማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃጽዮን በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሥርዓቱ የሚሳተፉ አካላትን ሥልጣንና ኃላፊነት በግልጽ በመዘርዘር፣ የአገልግሎቱን የሙያ ነፃነት ይበልጥ በማጠናከር በስታቲስቲክስ ሥርዓቱ የምንከተላቸውን መርሆችና አሠራሮች በግልጽ የሚደነግግ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲሁም በስታቲስቲክስ ረገድ የመጡ አዳዲስ ለውጦችን ከቴክኖሎጂም ከሥነ-ዘዴዎችም አኳያ በአግባቡ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግሥት በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ እንዲያወጣና ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተገኙ የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት በበኩላቸው፤ ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

ረቂቅ አዋጁ የሙያ ነፃነት በመስጠት ከፍተኛ መጠን ያላቸውን መረጃዎች ለመተንተን ቴክኖሎጂ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት  መጠቀምን የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ በመሆኑ አስፈላጊና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ብሔራዊ ሥርዓት ሲዘረጋ የክልሎች ሥልጣን አይጋፋም ወይ? እንዴትስ ለማጣጣም ታስቧል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ክልሎች የራሳቸው የስታቲስቲክስ አዋጅ ቢኖራቸውም፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሲባል ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት የሚሠሯቸው ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች የተነሱ ጠቃሚ ሐሳቦችና አስተያየቶችም አዋጁ ሲወጣ በግብዓትነት እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ሥርዓት በመፍጠር ሥርዓቱን መምራት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት የሚረዳ ነው ብለዋል።

ለዚህም ቋሚ ኮሚቴው አዋጁ ጠንካራና ታማኝ የመረጃ ሥርዓት መዘርጋት በሚያስችል መልኩ ጸድቆ እንዲወጣ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም