የባዮ ጋዝ ማብለያ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የባዮ ጋዝ ማብለያ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ):- የባዮ ጋዝ ማብላያ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ባዮ ጋዝን በገጠሩ አካባቢ ለኃይል ምንጭነት የመጠቀም ልምድ ቢኖርም ቴክኖሎጂውን የማስፋፋትና የማስተዋወቅ ሥራ በበቂ ሁኔታ አልተሰራም።
ኢትዮጵያ ለዘርፉ ያላትን ትልቅ አቅም በተቀናጀ መልኩ በማስፋፋትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በተደረገው ጥረትም ከ51 ሺህ በላይ አባወራዎች የባዮ ጋዝ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የባዮ ጋዝ ልማት ታዳሽና ከብክለት የጸዳ መሆኑን አንስተው የከፍተኛ ትምህርትና የጤና ተቋማት ጭምር ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ለአብነት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተገነባው የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያ 300 ሜትር ኪዩብ ባዮ ጋዝ በማብላላት 20 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን በቀን 5 ቶን የአፈር ማዳበሪያ ማምረት ያስችላል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከኃይል ምንጭነት ባለፈ ለአካባቢው ለግብርና ልማት ውጤታማነት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል።