ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በመደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የከተማዋን የ2019 ዓ.ም ረቂቅ በጀትን ጨምሮ በተለያዩ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በዚም መሰረት በመጀመሪያ በገለልተኛ የግል ተቋም የተጠናዉን የከተማዋን ገቢ የማመንጨት አቅም ጥናት ላይ ተወያይቶ ጥናቱ ይበልጥ በሁሉም ባለድርሻ አካላት በዉይይት እንዲዳብር አቅጣጫ አስቀምጧል።

በሁለተኛ ደረጃ የ2019 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ ዓመት ረቂቅ በጀት 502.27 ቢሊዮን ብር ሆኖ ወደ ለከተማው ምክር ቤት እንዲመራ አቅጣጫ አስቀምጧል።


 

ይህ የሀብት ድልድል እና ምደባ በዋናነት የከተማ አስተዳደሩን የልማት ስትራቴጂዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማረጋገጥ፣ የነዋሪዉን የልማት ፍላጎትና የአገልግሎት አቅርቦት ለማሳደግ በተለይም የስራ እድል ፈጠራን ለሚያበረታቱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች (መንገድ፣ ዉሃ፣ መኖሪያ ቤት፣ ፅዳት፣ ትራንስፖርትና የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል)፣ እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ሚና ላላቸዉ ዘርፎች (ትምህርት፣ ጤና እና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚደረግ ድጎማ) መስፈርቶችና ታሳቢዎች መሰረት ያደረገ ነው።

በዚሁ መሰረት በከተማው አስተዳደር ለማዕከል ሴክተር ተቋማትና ለክፍለ ከተሞች ለመደበኛና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት ከተደለደለው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ፤ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው 71 በመቶ ለድህነት ቅነሳና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበ ሲሆን፣ ቀሪው 29 በመቶ ደግሞ ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ተደልድሏል።


 

በሶስተኛ ደረጃ በፍትህ ቢሮ ተዘጋጅቶ በቀረብዉ፤- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የብቃት መመዘኛ እና ማረጋገጫ ተቋም ስልጠና የተግባር አደረረጃጀት እና አሰራሩን ለመወሰን በተዘጋጀዉ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በአራተኛ ደረጃ ማዘጋጃ ቤታዊ ይዞታ አገልግሎት ክፍያ ማስፈፀሚያ ረቂቅ ደንብ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በአምስተኛ ደረጃ በመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸዉ ፕሮጀክቶች የቀረበ የመሬት ምደባ ላይ ተወያይቶ ካቢኔዉ ውሳኔ ማሳለፉን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም