ቀጥታ፡

የሳይበር ጥቃትን መከላከልና የሳይበር ዐውዱን ደህንነት ማረጋገጥ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ እንዲሁም ተቋማዊ ደህንነትን ለማስከበር ወሳኝ አቅም ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12 /2018 (ኢዜአ):-የሳይበር ጥቃትን መከላከልና የሳይበር ዐውዱን ደህንነት ማረጋገጥ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ እንዲሁም ተቋማዊ ደህንነትን ለማስከበር ወሳኝ አቅም መሆኑን የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡ 

የመከላከያ ሳይበር ማዕከል ከተለያዩ የሠራዊት ክፍሎች መልምሎ በመሠረታዊ ሳይበር ደህንነት አጠባበቅ ዙሪያ ያሰለጠናቸውን የሶስተኛ ዙር የሳይበር ምህዳር ዘቦችን አስመርቋል።  


 

ማዕከሉ ተቋማዊና ሀገራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።  

በምረቃው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ የሳይበር ጥቃትን መከላከልና የሳይበር ዐውዱን ደህንነት ማረጋገጥ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ እንዲሁም ተቋማዊ ደህንነትን ለማስከበር ወሳኝ አቅም ነው። 

ሳይበር የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና እንዳለው የጠቀሱት ዋና አዛዡ፣ ሰራዊታችን ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር እራሱን እየዋሃደ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


 

የመከላከያ ተቋም ከለውጡ በፊት በአየር ኃይልና በምድር ኃይል ብቻ የተዋቀረ እንደነበር ያስታወሱት ሌተናል ጄኔራሉ፤ ከለውጡ በኋላ ግን አደረጃጀቱን በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል በሀገሪቱ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ  ጥቃቶችን በብቃት ማክሸፍ ወደ ሚያስችል ደረጃ መሸጋገሩን አረጋግጠዋል። 

የሳይበር ጥቃት የጦር ሜዳውን የውጊያ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈታተን መሆኑን አመልክተው፤ ማዕከሉ የሳይበር ኃይሉን በብዛትና በጥራት በማብቃት ሀገራዊና ተቋማዊ ዲጂታል ሀብቶችን ነቅቶ የመጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።


 

የሳይበር ማዕከል ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ደረጄ ደመቀ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የሳይበር ደህንነት ምሰሶዎችን ለመጠበቅ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም በአሰራር ስርዓት ቀረጻና ዝርጋታ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። 

ተመራቂዎቹም በስልጠና ያገኙትን አቅም በቀጣይነት በማዳበር፣ ሀገራቸውንና ተቋማቸውን ከጠላት የጥላቻ እና አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎችና ጥቃቶች በመከላከል አስተማማኝ የዲጂታል ዘብ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

በማዕከሉ የሳይበር አሰራር ስርዓትና ስታንዳርድ ዝግጅት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ ደመላሽ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞቹ በተቋሙ ብቁ መምህራን አማካኝነት በመደበኛና በኮሪኩለም ስልጠናዎች ተገቢውን እውቀት አግኝተው ለምረቃ መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ተመራቂ አባላቱም ባገኙት ሙያዊ ስልጠና የተጣለባቸውን ሀገራዊና ተቋማዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም