ሚኒስቴሩ የሕብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ የሕብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያካሄደ ነው
አዳማ፣ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ በማቋቋም የሕብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው የባስኬት ፈንድ (Basket Fund) ፕሮግራም በ43 ከተሞች የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የማጠቃለያ አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፥ ሚኒስቴሩ የውሃ ልማት ፈንድ በማቋቋም የሕብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያካሄደ ነው።
በሀገሪቱ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በገጠርና በከተማ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴም የልማት አጋሮች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ለውሃ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከመንግሥትና ከልማት አጋሮች የተገኘውን ሀብት በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ በባስኬት ፈንድ ፕሮግራም በሰባት ክልሎች በሚገኙ በ43 ከተሞች በ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት የተካሄደው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።
የውሃ ፕሮጀክቶቹ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ከፈረንሳይና ከጣሊያን መንግሥታት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ከክልል መንግሥታትና ከከተሞች አስተዳደር ሀብትን በአንድ ቋት በማቀናጀት ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
በከተሞቹ በተገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶችም ለ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ ማድረስ መቻሉን አውስተዋል።
በሚኒስቴሩ የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዶጊሶ ጎና በበኩላቸው፤ ፈንዱ ከተቋቋመ 23 ዓመታት ማስቆጠሩን ገልጸው፥በረጅም ጊዜ ብድርና በአነስተኛ ወለድ የተገኘ ሀብትን በማስተባበር በውሃ ልማት ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
ባለፉት ዓመታት ባስኬት ፈንድን ጨምሮ በ115 ከተሞች የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ የተካሄደ ሲሆን በዚህም 8 ሚሊዮን ሰዎች የንጹሕ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
በባስኬት ፈንድ ግንባታቸው ከተጀመሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ውስጥ የ40 ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ጠቅሰው፥ የቀሪዎቹ ሦስት ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ይበቃሉ ብለዋል።
በከተሞቹ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ እና ምንጭ ማጎልበት ሥራ፣ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣የውሃ መስመር ዝርጋታና የውሃ ማከፋፊያ ቦኖዎች ግንባታ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት አጋር አካላት ተወካዮች በበኩላቸው፥የኢትዮጵያ መንግሥት በውሃ ልማት ፈንድ በኩል እየተገበረ በሚገኘው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ስኬታማነት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
እስካሁንም ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የውሃ ፕሮጀክቶችን በብቃት ለማስተዳደርና ለመምራት የሚያስችል የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከሰባት ክልሎችና ከ43 ከተሞች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የፈረንሳይ ልማት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና የጣሊያን የልማት ድርጅት ተወካዮች ተገኝተዋል።