በክልሉ የግብርና ግብአትና የማሽነሪ አቅርቦትን በማሳለጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ግብአትና የማሽነሪ አቅርቦትን በማሳለጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ወላይታ ሶዶ፣ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ግብአትና የማሸነሪ አቅርቦትን በማሳለጥ የግብርና ልማትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሁለገብ ሕብረት ሥራ ማህበራት ፌደሬሽን ምስረታ ጉባኤ ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) የሕብረት ሥራ ማህበራትን አቅም በማደራጀት የክልሉን አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
የግብርና ግብአትና የማሸነሪ አቅርቦትን በማሳለጥ የግብርና ልማትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተናግረዋል።
ይህን ለማጠናከር ፌደሬሽን ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፣ የፌደሬሽኑ መቋቋም የአርሶ አደሩን እንዲሁም የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የጎላ ድርሻ አለው ብለዋል።
የግብርና ምርትን ከማሳ እስከ ተጠቃሚዎች ለማድረስ እንዲሁም የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ግብአቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የፌደሬሽኑ መቋቋም ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉም አክለዋል።
የክልሉ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ይበልጥ ለማነቃቃት እንዲሁም የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት ይደግፋል ሲሉም መሪሁን (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
በክልሉ 6 ሺህ 381 መሰረታዊ እና 30 የሕብረት ሥራ ዩኒየኖች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ፎላ ናቸው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የሕብረት ሥራ ማህበራት በኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተቀረጸው የማሻሻያ ሪፎርም ውጤት እያስገኘ ነው።
የህብረት ሥራ የሪፎርም ትግበራ ከተጀመረ ወዲህ ዜጎች በህብረት ስራ የመደራጀት፣ የቁጠባ፣ የብድር ስርጭት መጠንና አመላለስ እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ግብይት መጠን እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በክልሉ 17 የሕብረት ሥራ ማህበራትን በማቀፍ የተመሰረቱ ዩኒየኖችን አቅም በማቀናጀት በሁለገብ ህብረት ሥራ ፌደሬሽን እንዲደራጁ መደረጉንም ጠቁመዋል።
ዛሬ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተው ፌደሬሽን የግብርና ግብአቶችንና ማሽነሪዎችን በማቅረብና ሜካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት በግብርና ልማት አርሶ አደሩን ያግዛል ብለዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው በሕብረት ስንቆም አቅማችንን አደራጅተን ለሀገር ዕድገትና ልማት የተሻለ ነገር መፍጠር እንችላለን ብለዋል።
በመሆኑም የዞኑን አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የተቋቋሙ ማህበራትን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ የክልልና የዞን ሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በወላይታ ሶዶ ከተማ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበራት የሥራ እንቅስቃሴም ተጎብኝቷል።