የአረንጓዴ አሻራ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃና ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት ትልቅ አቅም ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃና ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት ትልቅ አቅም ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12 /2018 (ኢዜአ):- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የግብርና ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃና ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት ትልቅ አቅም መፍጠሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች በተሳካ ሁኔታ ተተክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2018 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታላቅ ግብ ተቀምጦ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወቃል።
ይህ ንቅናቄ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ፣ አገራዊ መልክዓ-ምድርንና የማኅበረሰብ ሕይወትን በመቀየር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ ጸሐፊ ፋኖሴ መኮንን እንደገለጹት፤ መንግሥት የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ለማልማትና ለመንከባከብ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በስኬት ሲያከናውን ቆይቷል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የችግኝ ተከላ ተግባር 40 በመቶ የሚሆኑት ሀገር በቀል የደን ዝርያዎች ሲሆኑ፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ እንደ ፍራፍሬ፣ ቡና፣ የእንስሳት መኖ፣ ለአፈር ጤንነትና ለምነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ናቸው ብለዋል።
መርሃ ግብሩ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
ከተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ጋር ተቀናጅቶ መከናወኑም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና ከአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል ብለዋል።
ይህም የግብርና ምርትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደንና የግጦሽ መሬት ዕጽዋት ብዝሃ ሕይወት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ስዩም በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገር በቀል ዕጽዋት መልሰው እንዲያንሰራሩ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህ አገራዊ ተግባር በሀገሪቱ ተስማሚና ምቹ የአየር ሁኔታ እንዲኖር በማድረግ፣ በየአካባቢው ባሉ ሥርዓተ-ምህዳሮች ውስጥ የደን ሽፋን እንዲጨምርና የብዝሃ ሕይወት ሀብቶች በአግባቡ እንዲጠበቁ ማስቻሉን አብራርተዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚዎቹ እንዳሉት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሀገር ውስጥ ሁለንተናዊ ጥቅሙ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤትና ከዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ይህ አኩሪ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በ"አረንጓዴ ዲፕሎማሲ" በበጎ እንድትነሳ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡