ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር አንድነትን የሚያጠናክር ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር  አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሳሙኤል ዶ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ጉባኤውን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ጉባኤውን ለማካሄድ የሚያስችል አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች እያከናወነ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሳሙኤል ዶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ አስደናቂ ሥራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮችን በመመካከር በመፍታት ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር  የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የምክክር ሂደት በስኬታማነት በማስቀጠል ላሳዩት ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ኮሚሽኑ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የላይቤሪያን ተሞክሮ ጨምሮ በኮሎምቢያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያና በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች የተደረጉ ብሔራዊ ምክክሮችን ማጥናታቸውን ጠቅሰው፤ የምክክር ሂደት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

ይህ ዓይነቱ ሂደት ከፍተኛ ፍላጎትን፣ ትልቅ ቁርጠኝነትን እና በጋራ ወደፊት ለመራመድ ጠንካራ ፅናትን የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሰላማዊና የምክክር አማራጮች የማኅበረሰብን የጋራ መጻኢ ዕድል ይበልጥ ብሩህ እንደሚያደርጉ አስገንዝበው፤ በርካታ ብሔረሰቦችና አስደናቂ ታሪኮች ያላትን ኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ልማት ይበልጥ ለማጠናከር የጋራ ምክክር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በምክክር ሂደቱ በንቃት በመሳተፍ ለውጤታማነቱ ገንቢ ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም