በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል -ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል -ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩና ካቢኔያቸው በክልሉ በማዕድን ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አቶ ኦርዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በዘርፉ በተለይም በግራናይትና ላይምስቶን ምርት ያለውን እምቅ ሃብት ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎችም በርካታ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዘርፉ ያለውን ሃብት በአግባቡ መጠቀም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎችን ከማበረታታት ባሻገር፤ አዳዲስ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት።