በከተማ አስተዳደሩ ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የሰላም አሴት ግንባታ ስራዎች መልካም ውጤት አስገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አስተዳደሩ ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የሰላም አሴት ግንባታ ስራዎች መልካም ውጤት አስገኝተዋል
ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፡-በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ ዘላቂ ሰላምን የማጽናትና ህግ የማስከበር ተግባራት ከተማዋ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ተመራጭነቷን እንድታስቀጥል እድል መፍጠራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ዳንኤል እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ህዝቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የሰላም አሴት ግንባታዎች መልካም ውጤት አስገኝተዋል።
በዚህም ከሀይማኖት መሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች በሰላም ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም በመውሰድ በቅንጅት ለመስራት ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ ያለውን ዘላቂ ሰላም በማጽናት የኮሪደር ልማት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ሌሎች የመሰረተ ግንባታዎችን በማፋጠን የከተማዋ እድገት እንዲፋጠን ማስቻሉን ጠቁመዋል።
ይህም ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት ከተማዋ ለኢንዱስትሪ፣ ለኢንቨትስትመንት፣ ለቱሪዝምና ለንግድ የስበት ማዕከል ሆና እንድትቀጥል ማስቻሉን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በሚካሄዱ የልማት ስራዎችና በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በመደራጀት ወጣቶችን ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ያስቻለውም ህዝቡ ለሰላምና ልማት ያለውን ጽኑ አቋም የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በቀጣይ አጠናክሮ በማስቀጠል የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎችም በሰፈርና አካባቢ አደረጃጀት በመፍጠር የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው በመጠበቅ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ አለሜ በላይ እንደገለጹት የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ ለልማት ስራው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው የልማት ስራዎችም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በመሆናቸው የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።