ቀጥታ፡

ኤጀንሲው የጀመረው የኦንላይን አሰራር አገልግሎት አሰጣጥን ግልጽና ቀልጣፋ የሚያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2018(ኢዜአ)፦ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የጀመረው የኦንላይን አሰራር አገልግሎት አሰጣጥን ግልጽና ቀልጣፋ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡

የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ነዋሪዎች ባሉበት ሆነው የሚስተናገዱበትን የኦንላይን መተግበሪያ አስጀምሯል፡፡


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት፤ የኦንላይን አገልግሎቱ የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽና ቀልጣፋ የሚያደርግ ትልቅ ሥራ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በከተማው እየተሰጡ የሚገኙትን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ግልጽ የማያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

መተግበሪያው በሀገር በቀል አቅም በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ መሆኑ ትልቅ ኩራት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው የጀመረውን የአሠራርና የሪፎርም ሥርዓት አጠናክሮ ቀጥሏል።


 

ዛሬ በይፋ የተጀመረው የኦንላይን አገልግሎትም የዚሁ የሪፎርም ስራ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ቀልጣፋ እና ምቹ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህም የከተማዋ ነዋሪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው የልደት ካርድ፣ የመታወቂያ አገልግሎት እና ያላገባ ማረጋገጫን በኦንላይን በመጠየቅ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት አሰራር እንደሆነ አመልክተዋል።

በተጨማሪም አዲሱ የኦንላይን መተግበሪያ የሐሰተኛ ሰነዶችንና የሐሰተኛ ማንነቶችን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በኩል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ መተግበሪያው አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሳልጥ ትልቅ ተቋማዊ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም