ቀጥታ፡

የቡናን ጣዕም የሚያስጠብቁ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ይጠናከራሉ

ሃዋሳ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦የቡናን ተፈጥሯዊ ጣዕም የሚያስጠብቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በሲዳማ ክልል ቨርሚ ኮምፖስት በዘመናዊ መንገድ አዘጋጅቶ መጠቀም ላይ ለልምድ ልውውጥ የተዘጋጀ መድረክና የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የቡናን ተፈጥሯዊ ጣዕም ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው። 

ባለስልጣኑ በቡና ግብይትና ልማት ላይ አዳዲስ የሪፎርም ሥራዎችን መጀመሩ የቡና ምርታማነትና ጥራትን በማስጠበቅ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነውን የኢትዮጵያን ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕም የሚያስጠብቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።   

ለእዚህም በክልሎች ያለውን ተሞክሮ የመቀመር ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ነው የገለጹት።

በተለይ በሲዳማ ክልል ቡና የሚያዘጋጁ ኢንዱስትሪዎችን ከአርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር የተጀመረው የቨርሚ ኮምፖስት አጠቃቀም የቡናን ጥራት ለማስጠበቅ የጎላ ድርሻ ስላለው በሌሎች ክልሎችም ይጠናከራል ብለዋል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታጋይ ኑሩ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የቡናን ጥራትና ምርታማነት ለማስጠበቅ የተቀረጹ ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ ተፈጥሯዊ ጣዕሙን የጠበቀ ቡና እየተመረተ  ነው።

ለዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን የማጠናከር ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፣ ቨርሚ ኮምፖስት በሲዳማ ክልል ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ አዲስ ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቨርሚ ኮምፖስትን ጨምሮ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በእያንዳንዱ አርሶ አደር ማሳ በማዘጋጀት ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውንና ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ ቡና የማቅረብ ተግባር ይጠናከራል ብለዋል፡፡

በክልሉ በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች እና በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ የተጀመረው የቨርሚ ኮምፖስት ዝግጅትና አጠቃቀም የቡና ጥራትና ምርታማነትን አሳድጓል ያሉት ድግሞ የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ናቸው፡፡

የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀረጹ 12 ፓኬጆች እንዳሉ ጠቅሰው፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥቅም ላይ የዋላው የቨርሚ ኮምፖስት በ45 ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ የሚደርስ፣ ጊዜን እና ጉልበትን የሚቆጥብ ነው ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ፣ በሲዳማ ክልል ቨርሚ ኮምፖስት በዘመናዊ መንገድ የማዘጋጀት ሥራ ልምድ ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የቡና ኢንዱስትሪዎችን ከአርሶ አደሩ ጋር የማስተሳሰር ተሞክሮው መስፋት ስላለበት በክልላቸው እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡

በዳሌ ወረዳ ሾኢ ቀበሌ በቨርሚ ኮምፖስት አዘገጃጀት ተሞክሯቸውን ያካፈሉት የተደራጁ ወጣቶች በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኮምፖስቱን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል።

ባለስልጣኑ በሲዳማ ክልል በአርሶ አደሮችና በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ያለውን የቨርሚ ኮምፖስት አዘገጃጀት ልምድ ለመለዋወጥ ባዘጋጀው ጉብኝት ላይ ከ5 ቡና አብቃይ ክልሎች የመጡ አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም